ቀጥታ፡

ደም በመለገስ የሰው ልጆችን ህይወት መታደግና የሰብአዊ አገልግሎትን ማጠናከር ይገባል-አገልግሎቱ

ሰመራ፤ሚያዝያ 3/2017 (ኢዜአ) ደም በመለገስ የሰው ልጆችን ህይወት መታደግና የሰብአዊ አገልግሎትን ማጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ የደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ።

አገልግሎቱ በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው፤ በደም ዕጦት ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች እየተሰቃዩ የሚገኙ ወገኖችን ደም በመለገስ ልንደርስላቸው ይገባል።

በአፋር ክልል በዘርፉ እየተሰራ ያለው ተግባር በጎ መሆኑን ጠቅሰው፥ በባንኮች ውስጥ ግን ደም እንዲኖር የህብረተሰብ ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የወጣቶች ባህልና ሰፓርት ቢሮ ኀላፊ አቶ ሐሚድ ዱላ እንዳሉት ደም መሠብሰብ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ይሰራል።

በየደረጃው በሚገኙ አካላት ትኩረት በማድረግ ንቅናቄዎቹ እንዲጠናከሩ ይደረጋልም ብለዋል።

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ በበኩላቸው እንደተናገሩት በክልሉ ደም በተገቢው መሠብሰብ እንዲቻል የንቅናቄ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በዚህም ከሠመራ በመቀጠል በአዋሽ ሰባት እንዲሁም በአብአላ ከተሞች እንደሚቀጥል በማውሳት።

አሁን ላይ በክልሉ ያለው ደም የመለገስ ኹነት አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው ባለድርሻ አካላት፣ የሐይማኖት አባቶችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም