ቀጥታ፡

ከፍተኛ በጀት የወጣባቸው መሰረተ ልማቶች የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው-ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 3/2017(ኢዜአ)፦ ከፍተኛ በጀት ወጥቶባቸው የተሰሩ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆን እንደሚገባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የፌደራል ዋና ኦዲተር የ2014 የክዋኔ ኦዲትን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በድሬዳዋ-ደወሌ ቅርንጫፍ የኢንተርፕራይዙን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክቷል።

ከተቋሙ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋርም ውይይት አድርጓል።

የቋሚ ኮሚቴው የመስክ ምልከታ ቡድን አስተባባሪ አቶ ደረጄ ዱባለ፤ በኢንተርፕራይዙ የተጀመሩ መልካም ተግባራትን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርአትን በመከተል የተከናወኑ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን አመልክተዋል።

በኢንተርፕራይዙ ለአሰራር ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በመለየት ውጤታማነትን ይበልጥ ማረጋገጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው፤ የድሬዳዋ-ደወሌ የክፍያ መንገድ ካለው ሀገራዊ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር መስመሩን በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና ብቃት ባለው የሰው ኃይል የተደራጀ እንዲሆን ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንተርፕራይዙ ለተገልጋዮች ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎቶችን የሚሰጥ እና የሚሰበስበውን ገቢ ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የድሬደዋ-ደወሌ የክፍያ መንገድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሮብሌ አሊ ሀራድ፣ ቅርንጫፉ ደህንነቱ የተጠበቀ ምቹ ዘመናዊና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የተሻሻሉ አዳዲስ የውስጥ የአሰራር ስርአቶችን ወደ ስራ ማስገባቱን ገልጸዋል።

በዚህም የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉንም ነው የተናገሩት።

በድሬደዋ-ደወሌ የክፍያ መንገድ ለሚያጋጥሙ የተለያዩ አደጋዎች ፈጣን ግብረ- መልስ ለመስጠት የሚያስችሉ ማሽነሪዎች ተገዝተው ወደ ስራ መግባታቸውንም ጠቁመዋል።

የመንገድ ወሰንን ማስከበር የካሳ ክፍያ እና የመብራት ኃይል አቅርቦት ተግዳሮቶች እንዲፈቱ ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም