ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቀጣናውን ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስር ለማጎልበት የጎላ ሚና ይኖረዋል -የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 3/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጎልበት የጎላ ሚና እንደሚኖረው የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ በረከት ድሪባ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ በረከት ድሪባ ለኢዜአ እንዳሉት፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የልማት እድሎችን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትና ውሕደትን ያሳልጣል።

ግድቡ የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በተለይም የኤሌክትሪክ ሃይል መሠረተ ልማት ዝርጋታን ለማሻሻል የሚረዳ ወሳኝ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ግድቡ የተሻሻለ የሃይል አቅርቦትን በማጎልበት የቀጣናውን ውህደት ለማፋጠን የሚረዳ ሲሆን በሚያመነጨው የኤሌክትሪ ሀይል ለአካባቢው አገራት የትብብርና የልማት እድሎችን እንደሚከፍትም ጠቅሰዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያ ቀጠናውን በኃይል ለማስተሳሰር እያደረገች ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያሳድግና ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ በቀጠናው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የኢንቨስትመንት አማራጭን ሊጨምር እንደሚችልም አንስተዋል።

የግድቡ ግንባታ በቀጣናው የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረትን በመቅረፍ ለኢንዱስትሪ ልማት ምቹ እድል ይዞ ከመምጣት ባለፈ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ እንደሚረዳም ነው የተናገሩት።

የግድቡ ግንባት የቀጣናው አገራት የመልማት አቅማቸውን እንዲጠቀሙ በማድረግም ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉም እንዲሁ።

በዚህም በአካባቢው ያሉ ጎረቤት አገራት የኢትዮጵያን የልማት ስራዎች በመደገፍ የጋራ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድጉ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።

በዋናነትም ከግድቡ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ምርትና ስርጭት ለቀጣናው የጋራ ተጠቃሚነትን ከማምጣት ባለፈ ኢኮኖሚውን ለማሳደግም እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በአካባቢው ያሉ ጎረቤት አገራት ያሏቸውን እምቅ የመልማት አቅም በመጠቀም ቀጣናውን ለማዋሕድ ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም