ቀጥታ፡

የምርት ብክነትን በመቀነስ የምግብ ዋስትና እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 3/2017 (ኢዜአ)፦ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምርት ብክነትን በመቀነስ የዜጎችን የምግብ ዋስትና እና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ትኩረት መደረጉን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የምርት ብክነትን ለመከላከል ከሰብል ስብሰባ ጀምሮ ምርቱ ጥቅም ላይ እስከሚውል ድረስ ዘመናዊ አሰራሮችን የመከተል ሂደቶች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑንም ተጠቁሟል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የምርት ብክነት እና ብክለትን ለመከላክል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከእርሻ እስከ ጉርሻ ባለው ሂደት ብክነትን መከላከል እንደሚገባ ጠቁመው፤ በእነዚህ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ይህም የዜጎችን የምግብ ዋስትናና ዘላቂ ልማት በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ዓይነተኛ ሚና እንዳለውም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

መንግስት ምርታማነትን ለማሳደግ በሰጠው ትኩረት የግብርና መካናይዜሽንን ማሳደግ፣የግብዓት አቅርቦቶችን ማስፋት ላይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመዋል፡፡

ተዛማች ተባዮች የሚያደርሱትን ጉዳቶች ለመከላከልና የምርት ብክነትን ለማስቀረት ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ መንግስት አምስት ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመግዛት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱንም ተናግረዋል፡፡

በምርት መሰብሰብ ወቅት ለምግብነትም፣ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ እንዲሁም ለውጭ ገበያም የሚላኩ ምርቶች በጥራትና በተገቢው መጠን ሳይባክኑ መሰብስብ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የምርት ብክነትን ለመከላከል የምርት ስብሰባን በዘመናዊ መልኩ ማካሄድ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም የሚሆኑ የመካናይዜሽን መሳሪያዎችንና መለዋወጫዎችን መንግስት ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡

ከምርት ስብሰባ በኃላ የሚያጋጥሙ የምርት ብክነትና ብክለትን ለመከላከል መንግስት የተለያዩ የድህረ-ምርት እንክብካቤ የሚደረግባቸው የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሮች እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም የብረት ጎተራዎችን እና አየር የማያስገቡ የተለያዩ መጠን ያላቸውን ቀረጢቶች መሰራጨታቸውን ገልጸው፤ ይህም የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ ሰፊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም