በከተማው የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ሚናችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ሚናችንን እንወጣለን
ወልዲያ፤ሚያዝያ 2/2017 (ኢዜአ)፡-በከተማው የብልጽግና ፓርቲንን የአሠራር መመሪያና ሥነ-ምግባርን በማክበር ቀጣይ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ሚናቸውን እንደሚወጡ በወልዲያ ከተማ አስተዳደር የአመራር አባላት ገለጹ።
በተሻሻለው የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት፣ የአሠራር መመሪያና በኢንስፔክሽን ሥነ-ምግባር ኮሚሽን መተዳደሪያ ደንብ ዙሪያ ዛሬ ለአመራር አባላት በወልድያ ከተማ ዛሬ ሥልጠና ተሰጥቷል።
ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል በወልድያ የየጁ ክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚ አቶ ይመር አየለ፤ፓርቲው ባስቀመጠው ሥነ ምግባርና መርህ መሰረት ያደረገ አደረጃጀትና አሰራር በመዘርጋት ቀጣይነት ያለው ለውጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለዚህም የፓርቲው አደረጃጀትና የአሠራር መመሪያ ተሻሽሎ መቅረቡ አመራሩና አባላቱ ለመርህ ተገዥ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የተሻሻሉ አሠራርና መመሪያዎችን ተቀብሎ ወደ ሥራ መግባት ከጠንካራ ፓርቲ አመራር የሚጠበቅ ነው " ያሉት ደግሞ በአስተዳደሩ የታላቁ ራስ ዓሊ ክፍለ ከተማ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ከድር ነጋሽ ናቸው።
ፓርቲው ያሻሻላቸው የአደረጃጀትና የአሠራር መመሪያዎች ወጥነት ያለው አመራር በመስጠት በየዘርፉ የሕዘብ እርካታን ለመፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል።
"ጠንካራ ፓርቲና መንግስት ለመገንባት የአሠራር ማሻሻያው አስፈላጊ ነው" ያሉት ደግሞ ጽሁፍ ያቀረቡት በብልጽግና ፓርቲ የወልዲያ ከተማ አስተዳደር የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ብዙዬ ጫኔ ናቸው።
በዚህም የሥልጠናው ተሳታፊ አመራርና አባላት የፓርቲውን ስነ-ምግባርና መርህ የማክበር ጉዳይ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግደታም ጭምር መሆኑ ተገንዝቦ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በየደረጃው ሙስናና ብልሹ አሠራርን ታግሎ ከምንጩ ለማድረቅ የሚያስችል መርህ በመዘርጋትና ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ከሁሉም ሠልጣኝ የሚጠበቅ ነው ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የከተማ አስተዳደሩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ገብሬ በበኩላቸው፤ ፓርቲው ያሻሻላቸው የአደረጃጀትና የአሠራር መመሪያዎች ላይ አመራሩ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ለተግባራዊነቱ ጠንክሮ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።
የፓርቲዉን የአሠራር መመሪያና ሰነ-ምግባርን በማክበር የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የአመራር ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የአመራር አባላቱ ገልጸዋል።
በሥልጠናው ላይ የከተማ አስተዳደሩ ፣ የክህለ ከተሞችና ቀበሌ አመራር እና አባላት ተሳትፈዋል።