ከ338 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ህገ ወጥ መድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ተይዘዋል - ኢዜአ አማርኛ
ከ338 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ህገ ወጥ መድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ተይዘዋል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 2/2017(ኢዜአ):-ከ338 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ህገወጥ የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች መያዛቸውን የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።
ከህገወጥ ድርጊቱ ጋር በተያያዘ 19 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑም ተገልጿል።
ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ህገ ወጥ የመድሃኒት ዝውውር ላይ ባሳለፍነው ሳምንት በአዳማና በአዲስ አበባ ከተሞች በ23 ቦታዎች በሰራው የቁጥጥር ስራ በተገኙ ውጤቶች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም ወልዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በተደረገው የቁጥጥር ስራ ግምታዊ ዋጋቸው 118 ሚሊየን ብር የሆነ መድሃኒቶች ተይዘዋል።
ግምታዊ ዋጋቸው 150 ሚሊየን ብር የሆነ ጥቅም ላይ የማይውሉ የህክምና መሳሪያዎች እንዲሁም 70 ሚልየን ብር የሚገመቱ ተገቢው የጥራት ምርመራ ያልተደረገላቸው የህክምና መሳርያዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።
ምርቶቹ የመጠቀሚያ ጊዜ አልፎባቸው እንደአዲስ የመጠቀሚያ ጊዜ የተለጠፈባቸው መድኃኒቶች፣በባለስልጣኑ ያልተመዘገቡና የገበያ ፍቃድ የሌላቸው ህገወጥ የጤና ግብዓቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል።