ቅርሶችን በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
ቅርሶችን በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ባለስልጣኑ
ዲላ፤ ሚያዚያ 2/2017(ኢዜአ)፡- ቅርሶችን በዩኔስኮ ከማስመዝገብ ባሻገር በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ።
በኦሮሚያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ቅርሶችን ማስተዋወቅ ዓላማ ያደረግና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ያሳተፈ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ጉብኝት እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌታቸው ረብራ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በተጎበኘበት ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ቅርሶች የሀገር አሻራና የማንነት መገለጫ ከመሆናቸው ባሻገር የቱሪዝም ሃብት ናቸው።
ከብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፎች ቱሪዝም አንዱ መሆኑን አስታውሰው ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በመንከባካብና በማልማት የቱሪዝም አቅማቸውን በአግባቡ ለመጠቀም እየተሰራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ 18 የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚና በርካታ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ባለቤት መሆኗንም አንስተዋል።
ቅርሶችን በዩኔስኮ ከማስመዝገብ ባሻገር በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ጉብኝቱም ይህንኑ ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
ቅርሶችን ጠብቆ ለትውልድ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
ቅርሶችን ለመጠበቅና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ ማስተዋወቅ መሰረታዊ ጉዳይ ነው ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ደርቤ ጅኖ ናቸው።
የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና ታዋቂ ግለሰቦችን በመጠቀም የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርን የማስተዋወቅ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ36ሺህ 200 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ቅርሱን መጎብኘታቸውን አንስተው፣ ይህም ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል ጋዜጠኛ አስቻለው ጌታቸው በበኩሉ ጉብኝቱ ስለሀገራችን ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም አቅም ተጨማሪ ግንዛቤ እንድንጨብጥ ያስችላል ብሏል።
ይህም በሙያው ቅርሶችን በማስተዋወቅ የህብረተሰቡን የጉብኝት ባህል ለማሳደግ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁሞ፣ በተለይ ቅርሶች ተጠብቀው እንዲለሙ በማድረጉ በኩል የሚዲያ ባለሙያዎች ሚናችንን ልንወጣ ይገባል ነው ያለው።
በጉብኝቱ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር፣ መልካ ቁንጡሬንና የባሌ ተራሮችን እንዲሁም ጢያ ትክል ድንጋይን ጨምሮ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች የተካተቱ ሲሆን የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎችም በመሳተፍ ላይ ናቸው።