ቀጥታ፡

ባለስልጣኑ የስንዴ ዱቄት ማበልጸግ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የቁጥጥር ሥርዓት እንዲተገበር አሳሰበ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 2/2017(ኢዜአ)፡- ጤናማና አምራች ትውልድ ለማፍራት የስንዴ ዱቄት ማበልጸግ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የቁጥጥር ሥርዓት እንዲተገበር የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አሳሰበ።

ያልተመጣጠነ ምግብ መመገብ በሰዎች ጤናና አእምሮ ዕድገት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ።

በኢትዮጵያ ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራት ህብረተሰቡ በዕለት ተዕለት የሚጠቀማቸው የምግብ ዓይነቶች በንጥረ ነገር የበለጸጉ እንዲሆኑ አስገዳጅ መመሪያ ወጥቷል።

ከእነዚህም መካከል የምግብ ዘይትና የስንዴ ዱቄት ዋነኞቹ ናቸው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን የሥራ ሃላፊዎች እንደገለጹት፤ ይህ ውሳኔ ጤናማ፣ ንቁና አምራች ዜጋ ለማፍራት በሚደረገው ጥረትና ለሀገር ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።

በባለስልጣኑ የምግብ ምዝገባና ፍቃድ መሪ ሥራ አስፈፃሚ መንግስቱ አስፋው፤ ዘይትና የስንዴ ዱቄት በንጥረ-ነገር እንዲበለፅጉ በደረጃዎች ምክር ቤት ውሳኔ ተሰጥቶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

በምርቶቹ ላይ አስገዳጅ መመሪያ መውጣቱን ተከትሎ ባለስልጣኑ ፍቃድ ለሰጣቸው አምራቾች የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ሲሰጥ መቆየቱንም ገልጸዋል።

በባለስልጣኑ የምግብ ኢንስፔክሽንና ሕግ ማስፈፀም መሪ ስራ አስፈፃሚ ሙላቱ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ለህብረተሰቡ ጤናና ምርታማነት ሲባል ሁሉም ዓይነት የምግብ ዘይትና የስንዴ ዱቄት መበልጸግ እንዳለበት አስረድተዋል።

ይሁንና አምራቾች የተሰጣቸውን የዝግጅት ጊዜ ቢጨርሱም ሙሉ ለሙሉ ወደ ትግበራ ባለመግባታቸው ቁጥጥር እየተደረገ በየጊዜው ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸው እንደሚገኝ ነው ያነሱት።

ያልበለፀገ የስንዴ ዱቄት በህብረተሰቡ ጤና ላይ ሊያደርስስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጣውን መመሪያ በእኩል ደረጃ እንዲተገበርም ነው የሥራ ኃላፊዎቹ ያሳሰቡት።

የስንዴ ዱቄት ማበልጸግ ላይ በባለስልጣኑ ፍቃድ የወሰዱ አምራቾች ጥቂቶች መሆናቸውንና አብዛኞቹ ከክልል ጤና ቢሮ ፍቃድ ያገኙ ናቸው ብለዋል።

ለአብነትም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ400 በላይ የስንዴ ዱቄት አምራቾች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ወደ ማበለጽግ የገቡት ግን ጥቂቶች እንደሆኑ ገልጸዋል።

እንደ ባለስልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ፣ የስንዴ ዱቄትን ማበልፀግ ለህብረተሰብ ከሚሰጠው ጠቀሜታ አኳያ ሊተገበር ይገባል።

ባለስልጣኑ ፍቃድ የሰጣቸውን ድርጅቶች በየጊዜው ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ እየወሰደ ቢሆንም፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት ያለው የአተገባበር ስርዓት ባለመኖሩ ውጤቱ በሚፈለገው ልክ እንዳይሆን አድርጓል ነው ያሉት።

ተቆጣጣሪ ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ ለመመሪያው መተግበር የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

ባለስልጣኑ ያልበለፀገ የስንዴ ዱቄት ለህብረተሰቡ በሚያሰራጩ ድርጅቶች ላይ እየወሰደ ያለውን አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም