ቀጥታ፡

በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት አሳታፊና የሁሉም ሃሳብ እንዲካተት እየተደረገ ነው -- ኮሚሽኑ

ባህር ዳር ፤ሚያዚያ 2/2017(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት አሳታፊና የሁሉም ሃሳብ እንዲካተት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ገለጹ።

የአማራ ክልል የባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባስብ የምክክር ሂደት በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።


 

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ውልደማርያም፤ በሀገሪቱ በየጊዜው የሚገጥሙ ችግሮችን በሰለጠነና ዘመኑን በሚመጥን አግባብ ዘላቂነት ባለው መንገድ መፍታት ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ምክክር ወሳኝ መሆኑን አንስተው የምክክር ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት እለት ጀምሮ ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል።

ከዚህ በፊት በአብዛኞቹ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ስራ በስኬት መከናወኑን አስታውሰው በአማራ ክልልም በተመሳሳይ እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል።

የምክክር ሂደቱ በነፃነት፣ በአሳታፊነትና የሁሉም ሃሳብ ባካተተ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል እየተከናወነ ባለው የአጀንዳ ልየታ ህዝቡ በንቃት በመሳተፍ ለምክክር ያለውን ዝግጁነት በተግባር ማሳየቱን አድንቀው ለምክክሩ አጀንዳ አለኝ፤ ይካተትልኝ የሚለውን ሁሉ ለማስተናገድ ኮሚሽኑ ዝግጅ መሆኑን አረጋግጠዋል።


 

ሌላኛው የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በምክክር ሰላምን ማምጣት ልምድ ማድረግና የሚፈጠሩ ችግሮችን በስለጠነ መንገድ በመነጋገርና በመግባባት መፍታት ይገባል ብለዋል።

በክልሉ ጥያቄ አለን ብለው የሚንቀሳቀሱ አካላት ሁሉ ችግሮችን በዚሁ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ እንዲሆኑ ተደጋጋሚ ጥሪ እየቀረበላቸው መሆኑንም አንስተዋል።

ከሚያዚያ 2 እስከ 4/2017 ዓ/ም በሚቆየው መድረክ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ተፅኖ ፈጣሪ ግለስቦች፣ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፣ የመንግስት ተቋማት ወኪሎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም እየተሳተፉ ነው።

በአጀንዳ ማስባሰቡ ሂደት ክልሉን ወክለው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚከናወነው የምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ውኪሎች የሚመረጡ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም