ኢትዮጵያ በደኅንነትና በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ያሳየችው እመርታ ለአፍሪካዊያን ተምሳሌት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በደኅንነትና በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ያሳየችው እመርታ ለአፍሪካዊያን ተምሳሌት ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በደኅንነትና በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ያሳየችው እመርታ ለአፍሪካዊያን ተምሳሌት መሆኑን የናይጄሪያ የመከላከያ መረጃ ዋና ኃላፊ ገለጹ ።
በናይጄሪያ የመከላከያ መረጃ ዋና ኃላፊ ፓርከር አንዳያዳይ የተመራ ወታደራዊ ልዑካን ቡድን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትንና በቅርቡ የተመረቀውን የስካይ ዊን ኤሮናቲክስ ኢንዱስትሪን ጎብኝተዋል።
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለኢዜአ በላከው መረጃ እንዳመለከተው የናይጄሪያ የመከላከያ መረጃ ዋና ኃላፊ ፓርከር አንዳያዳይ፤ የስካይ ዊን ኤሮናቲክስ ኢንደስትሪ ፕሮጀከት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን ነው ብለዋል።
ይሔም በዘርፉ ከሌሎች ክፍለ ዓለማት ጥገኝነት ለመላቀቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል፡፡
የስካይ ዊን ኤሮናቲክስ ኢንደስትሪ ፕሮጀከት ብሔራዊ ደኅንነትንና ጥቅምን በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት እንዲሁም ሉዓላዊነትንም ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ የናይጄሪያ የመከላከያ መረጃ ዋና ኃላፊ ገልጸዋል።