ቀጥታ፡

በደብረ ማርቆስ ከተማ ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል

ደብረ ማርቆስ ፤ሚያዚያ 1/2017 (ኢዜአ)፡- የአካባቢውን ሰላም ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ በሰላምና ልማት ግንባታ ዙሪያና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ዛሬ ውይይት አካሄዷል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነትና የአደረጃጀት አማካሪ አቶ መልካሙ ሽባባው በውይይቱ ላይ እንደገለጹት የከተማዋን ሰላም በመጠበቅ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች የመለሱ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

ለአብነትም እየተከናወኑ የሚገኙት የደብረ ማርቆስ የአውሮፕላን ማረፊያ ፣ከ3 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ፣ የአውቶቢስ መናኸሪያና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነቡት የመስሪያና የመሸጫ ሼዶች፣ የኮሪደር ልማትና ሌሎች የልማት ስራዎች እንደሚገኙበት አክለዋል።

የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልም የከንቲባ ችሎትን በማቋቋም የቆዩ ችግሮች ሁሉ እየተፈቱ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል።

ዘላቂ ሰላምም ሆነ ልማት ሊመጣ የሚችለው ህብረተሰቡና መንግስት ተቀናጅተው ሲሰሩ ነው ያሉት አማካሪው በቀጣይ የተጀመረው ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል  ብለዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ንብረት ካሳ፤ የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ በሰፈራቸው አደረጃጀት ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል።

በአካባቢያቸው አዲስ ጉዳይ ሲያጋጥማቸውም ለሚመለከተው የመንግስት አካል በማሳወቅ ችግር ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል  እየሰሩ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ቢያድጌ ያዜ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ ያስጀመራቸውን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሰላም ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት ብለዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የተፈጠረውን አደረጃጀት በማጠናከር የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም