ቀጥታ፡

በባህርዳር የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት ህዝቡ በነቃ ተሳትፎው ቁርጠኝነቱን አሳይቷል

ባህርዳር፤ ሚያዚያ 1/2017(ኢዜአ)፡- በባህር ዳር ከተማ ሲከናወን በቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ሕዝቡ ያሳየው የነቃ ተሳትፎ ችግሮችን በመመካከር ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል ሲሉ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) ገለጹ።

በባህርዳር ከተማ ከመጋቢት 27 እስከ ሚያዚያ 1/2017 ዓ.ም ሲከናወን የቆየው የመጀመሪያው ዙር የአጀንዳ ማስባስብ ስራ በስኬት መጠናቀቁን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ይህን ተከትሎ ለመገናኛ ብዙህን መግለጫ ተሰጥቷል።

መግለጫው ከሰጡት መካከል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) ፤ የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ተወካዮች በባህር ዳር ከተማ ያከናወኑት የአጀንዳ ማስባስብ ተግባር በስኬት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ተወካዮቹ የክልሉን ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች በዝርዝርና በጥልቀት ያለምንም ገደብና ክልከላ ማቅረብ ችለዋል ሲሉ ገልጸዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰቡ ሂደቱ የታየው የነቃ ተሳትፎ ሕዝቡ ችግሮችን በመነጋገርና በመመካከር ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል ብለዋል።

ሃገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት፣ዘላቂ ሰላም፣ መግባባትና ምክክር ባህል እንዲሆን በማድረግ አዲስ ምዕራፍ የታየበት ነውም ብለዋል።

ለአጀንዳ ማስባስብ ሂደቱ መገናኛ ብዙሃን ለተወጡት ገንቢ ሚና በምክክር ኮሚሽኑ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ሌላው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው፤ በባህርዳር ከተማ የተከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ውኪሎች ግልፅነት በሰፈነበት ሁኔታ መፈታት ያለባቸውን አጀንዳዎች በማቅረብ ለሃገራቸውና ለሕዝባቸው ያላቸውን ተቆርቋሪነት በተግባር አሳይተዋል ብለዋል።

ሃገር እንድትፀና ያላቸውን ቁርጠኝነት ባካሄዱት ጠንካራ ተሳትፎ አረጋግጠዋል ብለዋል።

ወኪሎቹ አጀንዳቸውን ከማስያዝ ባለፈ ቀጣይ የሚወያዩ 270 ወኪሎችን የመረጡ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የክልሉ የአጀንዳ ማሰባስብ ሂደት ተሳታፊ የህብረተሰብ ወኪሎች ሀሳባቸውን በነፃነት በማቅረብ በንቃት እንደተሳተፉ ቀደም ሲል መዘገባችን ይታወሳል።

#Ethiopian_News_Agency
#ኢዜአ #Ethiopia #ምክክር

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም