ቀጥታ፡

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር መሃሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 1/2017(ኢዜአ)፦ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር መሃሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

አፍሪካ ሕብረት እና በተመድ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር መሃሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል፡፡

የአዲሱ ሊቀ-መንበር መሃሙድ አሊ ዩሱፍ የስራ ዘመን ውጤታማ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው በውይይቱ ወቅት ፕሬዚዳንት ታዬ መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ሊቀ-መንበሩም ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ቀደም ሲል የነበረው የሕብረቱ አመራር የሰራቸውን ስራዎች በማስቀጠልና ለማጠናከር ትኩረት የሚሰጧቸውን ጉዳዮች በማንሳትም መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን አዲሱ ሊቀ-መንበር መሃሙድ አሊ ዩሱፍ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ስላላት ግንኙነት እና በአህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ጋር በአህጉሪቱ ወሳኝ እና ወደ ፊት በሚወስዱ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ እና በሕብረቱ መካከል ያለውን ጠንከራ ግንኙነት ለማስቀጠል እንደሚሰሩም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም