ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዘላቂ ልማት ፎረም ላይ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 1/2017(ኢዜአ)፦በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህልና ስፖርት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ቀጄላ መርዳሳ የተመራ ልዑክ በዩጋንዳ እየተካሄደ ባለው 11ኛው የአፍሪካ ክልላዊ የዘላቂ ልማት ፎረም ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

የዘላቂ ልማት ፎረሙ ዛሬ ተጀምሯል።

ፎረሙ የሚካሄደው“በዘላቂ እና ሁሉን አካታች የሳይንስ እና መረጃን መሰረት ባደረጉ መፍትሄዎች የስራ እድል ፈጠራ እና የኢኮኖሚ እድገትን በማፋጠን፤የ2030 እና 2063 አጀንዳዎችን እውን ማድረግ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከዩጋንዳ መንግስት ጋር በመተባበር ፎረሙን በጋራ አዘጋጅተውታል።

ኢትዮጵያ በሚኒስቴር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህልና ስፖርት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ቀጀላ መርዳሳ በተመራ ልዑክ ተወክላ እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መሪዎች ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችና እንዲ የተለያዩ ተቋማት በፎረሙ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።

የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ክቡር ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ ንግግር ባደረጉት ንግግር የአፍሪካን ዘላቂ ልማት ለማፋጠን፣ አፍሪካ የጥሬ እቃ አቅራቢ ከመሆን ተላቃ፣ በእሴት የዳበረ ውጤቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ እንደሚገባት ገልጸዋል።

ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ማጠናከርም የአፍሪካን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንደሚያፋጥንም አመልክተዋል።

ፎረሙ እ.አ.አ. በ2015 የጸደቀውን የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች እና የአፍሪካ የ2063 የአካታችና የዘላቂ ልማት አጀንዳዎች አፈጻጸም ይገመግማል ተብሎ ይጠበቃል።

በቀሪው የዘላቂ ልማት ግቦች የአምስት ዓመታት ትግበራን አስመልክቶ በተዘጋጀው የምክረ ሀሳብ ሰነድ ላይም ይወያያል።

ዘለቄታዊ እና አካታች እንዲሁም ሳይንሳዊና በመረጃ የተደገፈ መፍትሔ ለአፍሪካ 2063 የዘላቂ ልማት እቅድ መሳካት የተሰኘ የካምፓላ የውሳኔ ሀሳብ ሰነድ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ፎረሙ እስከ ሚያዚያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ በካምፓላ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም