ቀጥታ፡

ዴንማርክ በታዳሽ ኃይል እና በመጠጥ ውሃ አቅርቦት ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2017(ኢዜአ)፦የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በኢትዮጵያ ከዴንማርክ አምባሰደር ሱን ክሮግስትሩፕ ጋር በትብብር በሚሠሩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም፤ የዴንማርክ መንግሥት በዐቅም ግንባታ፣ በቴክኒካዊ ድጋፍ እና በታዳሽ ኃይል ልማት ኢንቨስትመንት ላይ በተለይም በንፋስ ኃይል ልማት በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በቆላማ እና ውኃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ላይ በሚተገበረው ፕሮግራም ላይም እንዲሳተፉም ጠይቀዋል።

አምባሰደር ሱን ክሮግስትሩፕ የዴንማርክ መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች በትብብር እየሠራ መሆኑን አንስተው፤ የአሰላ የነፋስ ኃይል ማመንጫ በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ የሚደረገው ትብብር ማሳያ ነው ብለዋል።

የዋሽ ፕሮግራምን በተለየ አቀራረብ ለመደገፍም ቁርጠኛ መሆናቸውን መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም