ቀጥታ፡

ችግሮችን በመመካከር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ሁሉን አካታችነትና መደማመጥ ወሳኝ ነው -ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)

ባህር ዳር፤ሚየዚያ 1/2017(ኢዜአ)፡-ችግሮችን በመመካከር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ሁሉን አካታችነትና መደማመጥ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

በክልሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የሚሳተፉበት አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ለመጀመር ዛሬ ቅድመ ውይይት ተካሄዷል።

በውይይት መድረኩ ላይ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር)፤ ለምክክሩ ስኬታማነት ሁሉም ያልተቆጠበ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የክልሉ የማህበረሰብ ተወካዮች አጃንዳ የማሰባሰብ ምክክር መካሄዱን ጠቅሰው፤ዛሬ ደግሞ የተፅዕኖ ፈጣሪ ግልሰቦችን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

ይህም የሁሉንም ሀሳብ በማካተት ሀገራዊ ችግሮችን በመነጋገር ለመፍታት የማመቻቸቱ ተግባር አካል መሆኑን አስረድተዋል።

ሃገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በመነጋገርና በመመካከር የመፍታት ሂደት እንደሆነ ገልጸው፥በዚህም አሸናፊው የሀሳብ የበላይነት ብቻ ነው ብለዋል።

ችግሮችን በመመካከር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ሁሉ አካታችነትና መደማመጥ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክክሩ በሀገሪቱ ችግሮች ከመፍታት ባለፈ አዲስ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል።

እንዲሁም የሀሳብ መሪዎችን ሚና በማጎልበት በሀገሪቱ ፍትህና ርትእ እንዲሰፍን ማድረግ እንደሆነም ገልጸዋል።

ሌላው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው፥ ምክክሩ ሀገርን የማፅናት ሂደት ነው፤ በሃገሪቱ አለመግባባትን መፍታት የሚቻለው በመመካከር ነው ብለዋል።

በዚህም የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለስቦች ያልተቆጠበ ተሳትፎ የማድረግ ሃላፊነታቸውን እንዲውጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም