በኦሮሚያ ክልል ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እየተከናወነ ያለው የሰላም ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እየተከናወነ ያለው የሰላም ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ጅማ፣መጋቢት 30/2017(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እየተከናወነ ያለው የሰላም ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ገለጹ።
በጅማ ከተማ "የሀይማኖት ተቋማት ሚና ለሳላም ግንባታና ለእርቅ" በሚል መሪ ሀሳብ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።
የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ መርዳሳ እንዳሉት፥ በክልሉ ህብረተሰቡን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በተከናወኑ የሰላም ግንባታ ሥራዎች ሰላም እየሰፈነ ነው።
ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተጀመረው የሰላም ግንባታ ሥራ በቀጣይም የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፥በ+ዚህ ሂደት የሀይማኖት ተቋማት ሚና የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
የሀይማኖት ተቋማት በህብረተሰቡ ውስጥ ሰላምና አንድነት እንዲጸና ያላቸው በጎ ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ ሰላሙን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል በሚሰራው ሥራ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የሀይማኖት ተቋማት እና አባቶች በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነት ተጠቅመው የታጠቁ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ የጀመሩትን ጥረት እንዲያጠናክሩም አስገንዝበዋል።
በመርሀ ግብሩ የተገኙት የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው፥የሀይማኖት ተቋማት ለዞኑ ዘላቂ ሰላምና ልማት ከፍ ያለ አስተዋጾ እያበረከቱ ነው።
በቀጣይም የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት አጠናክሮ ለማስቀጠል በጋራ መምከርና አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መተጋገዝ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በሰላም ኮንፈረንሱ የተሳተፉ የተለያዩ ሀይማኖት ተቋማት ተወካዮች በበኩላቸው፥ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀይማት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ጻሐፊ ሀጂ መስኡድ አደም ሀገራችን የብዝሀ ሀይማኖት ሀገር እንደመሆኗ በልዩነት ውስጥ የመከባበርና የወንድማማችነት እሴትን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሰላም ለሁሉም ማህበረሰብ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፥ የሀይማኖት ተቋማት ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የሰላም ኮንፈረንሱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ፥ የሀይማኖት ተቋማት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።
የሰላምና የፍቅርን ዘር በመዝራት በህብረተሰቡ ውስጥ ሰላምና አንድነትን ከማጽናት አንጻር የበኩላችንን እየሰራን ነው ብለዋል።
መርሀ ግብሩ ነገም የሚቀጥል ሲሆን በጅማ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ጉብኝትና ከህብረተሰቡ ጋር የሚደረግ ውይይት መኖሩም ተጠቁሟል።