የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ለጋዜጠኞች የሙያ ማረጋገጫ የመስጠት ኃላፊነት አልተሰጠውም - የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ለጋዜጠኞች የሙያ ማረጋገጫ የመስጠት ኃላፊነት አልተሰጠውም - የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2017(ኢዜአ)፦የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ለጋዜጠኞች የሙያ ማረጋገጫ የመስጠት ኃላፊነት አልተሰጠውም ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጋዜጠኞችን ወይም የሚዲያ ባለሙያዎችን የመመዝገብም ሆነ የሙያ ማረጋገጫ የመስጠት ተግባርና ኃላፊነት በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አልተሰጠውም ብሏል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ለጋዜጠኞች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት እና የጋዜጠኞች ምዝገባ ለማከናወን ውይይት እና እንቅስቃሴ መጀመሩን ደርሼበታለሁ ብሏል ባለስልጣኑ፡፡
ይሄንን ተከትሎም የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ጋዜጠኞችና የሙያ ማህበራት ጉዳዩን በተመለከተ የሕጋዊነት ጥያቄና ስጋቶቻቸውን ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ ብሏል ።
ምክር ቤቱ ጋዜጠኞችን ወይም የሚዲያ ባለሙያዎችን የመመዝገብም ሆነ የሙያ ማረጋገጫ የመስጠት ተግባርና ኃላፊነት እንዳልተሰጠውም ባለስልጣኑ አስታውቋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለዚህ የምክር ቤት ተግባር እውቅና የማይሰጥ መሆኑን ለማሳወቅ ይወዳል ሲል ገልጿል።