ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢና ሁለት አባላት እጩዎችን ከነገ ጀምሮ እንዲጠቁም ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2017(ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ እና ሁለት አባላት እጩዎችን ከነገ ጀምሮ እንዲጠቁም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስራ አመራር ቦርድ አባላት መልማይ ኮሚቴ ጥሪ አቀረበ።

የእጩዎች ጥቆማ መስጫ ጊዜ ከነገ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 21/2017 ዓ.ም እንደሚቆይም ኮሚቴው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 5/1/ እጩ የስራ አመራር ቦርድ አባላት መልማይ ኮሚቴ መቋቋም እንዳለበት ይደነግጋል።

በዚሁ መሰረት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢንና ሁለት አባላትን የሚመለምል ገለልተኛ ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።

የኮሚቴው ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ኮሚቴው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

በዚህም የውስጥ አሰራር መመሪያ፣ የድርጊት መርሀ-ግብር እንዲሁም የመመልመያ መስፈርት ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ኮሚቴው ግልጽ በሆነ አካሔድ እጩዎችን ለማቅረብ ይችል ዘንድ ይፋዊ የእጩዎች ጥቆማ ጥሪ ለመላው ህዝብ፣ ለፖለቲካ ድርጅቶች እና ለሲቪል ማህበረሰብ ያቀርባል ብለዋል።

በአዋጁ አንቀጽ 6(1) የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ሊያሟሏቸው ከሚገቡ መስፈርቶች አንጻር ለእጩነት የሚጠቁሟቸው ግለሰቦች መስፈርቶችን በሚገባ ማሟላታቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

‎ለእጩነት የሚጠቆሙ ግለሰቦች ዜግነታቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊ/ኢትዮጵያዊት መሆን አለባቸው ብለዋል።

ሌላኛው ከገለልተኛነት አንጻር የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆነ/ያልሆነች መሆን እንዳለበትም አመላክተዋል።

ከ‎ሙያዊ ብቃት አንጻርም ከምርጫ ጉዳዮች ጋር ተያያዥነት ባላቸው በተለይም በህግ፣ በፖለቲካል ሳይንስ፣ በሕዝብ አስተዳደር፣ በስታትስቲክስ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ተዛማጅነት ባላቸው ዘርፎች ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት ያለው/ ያላት መሆን እንዳለባቸው አንስተዋል።

መልካም ስነ-ምግባር እና ሰብዕና፣ ኃላፊነት የመሸከም ብቃት፣ ፍቃደኝነት፣ ተአማኒነት፣ ከሌሎች ጋር የመሥራት ከህሎት፣ የማስተባበር እንዲሁም በሥራቸው ላሉ ሠራተኞች እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ምቹ ሁኔታ የመፍጠር የተረጋገጠ ችሎታ እና ሌሎች ጠቃሚ ጉዳዮችን ይጨምራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እጩ ምክትል ሰብሳቢ እና አባላት ጥቆማ የሚቀርብበት ዘዴ በጽሁፍ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመሆኑም ጥቆማ አቅራቢዎች የሚከተሉትን የጥቆማ ማቅረቢያ መንገዶች መጠቀም እንደሚችሉም ተናግረዋል።

በኢሜይል‌‎ erc@hopr.gov.et

በዋትስ አፕ +251900357507

በ ቴሌግራም +251900357507

በፖስታ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ እጩ አባላት መልማይ ኮሚቴ የመልእክት ሳጥን ቁጥር 80001 ማቅረብ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በአካል ማቅረብ ለሚፈልጉ አራት ኪሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የእንግዳ መቀበያ ቢሮ በሚዘጋጅ ዝግ ሳጥን ውስጥ የጥቆማ ወረቀታቸውን ማስቀመጥ ይችላሉ ብለዋል።

ለበለጠ መረጃም በስልክ +251900357507 መረጃ ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ጥቆማ የሚቀርብበት የጊዜ ገደብን በተመለከተ ከነገ ሚያዚያ 1 እስከ ሚያዚያ 21/2017 ዓ.ም እስከ ቀኑ 11፡30 ለመልማይ ኮሚቴው ማቅረብ ይቻላል ብለዋል።

ከተቀመጠው የቀን እና ሰዓት ገደብ ውጪ የሚመጡ ጥቆማዎች ተቀባይነት እንደሌላቸውም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም