የአፍሪካ ሀገራት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሀገራት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሀገራት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ግጭትን አስቀድሞ ለመከላከል በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገለጹ።
የአፍሪካ የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት እና የአፍሪካ የጋራ ግምገማ ማዕቀፍ(APRM) አራተኛው የጋራ የትብብር ስብሰባቸውን ለሁለት ቀናት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ አካሂደዋል።
ስብሰባው የተካሄደው “መልካም አስተዳደር፤ ለአፍሪካ ግጭት መከላከል እና ዘላቂ ሰላም ምሰሶ ነው” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
ኢትዮጵያም በስብሰባው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች መወከሏን ኤምባሲው አስታውቋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት መልካም አስተዳደር ለማስፈን፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ለማጠናከር እና በሰላማዊ መንገድ ግጭቶች እልባት እንዲያገኙ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከአጀንዳ 2063 ጋር በተቆራኘ ሁኔታ የአፍሪካን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሰሩም አመልክተዋል።