ቀጥታ፡

በክልሉ የማዕድን ልማት አሰራሮችን በማሻሻል ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እያደገ ነው

መጋቢት 29/2017 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የማዕድን ልማት  አሰራሮችን በማሻሻል ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እያደገ መምጣቱን የክልሉ ማዕድን ልማት ባለስልጣን ገለጸ።

ከክልሉ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ወራት የተለያየ የማዕድናትን በብሔራዊ ባንክ በኩል ለውጪ ገበያ በማቅረብ 605 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱም ተገልጿል።

በተጨማሪም ለአገር ውስጥ ገበያ ከቀረበ የማዕድን ምርት ከ1 ቢሊየን 600 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ባለሥልጣኑ አስታውቋል። 

የኦሮሚያ ክልል ማዕድን ልማት ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ለሜሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉ መንግስት ለማዕድን ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ከዘርፉ ትልቅ ጥቅም እየተገኘ ነው።

በዚህም የማዕድን ዘርፉ በአግባቡ እንዲመራ ለማድረግ ደንቦች፣ ህጎችና መመሪያዎች ተዘጋጅተው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በተደረጉ ማሻሻያዎች ከማዕድን ሀብቱ ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ገልጸው ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ለሀገር ውስጥ ገበያ ከቀረበው የማዕድን ምርት 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እስከ አሁን 1 ቢሊየን 600 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ነው የገለጹት።

በክልሉ  የማዕድን ልማት ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት ባለፈ ለበርካታ ዜጎችም የስራ እድል እየፈጠረ መምጣቱንም አስረድተዋል።


 

በባለስልጣኑ የጂኦሎጂ ባለሙያ የሆኑት አቶ አለማየሁ ኦልጂራ በበኩላቸው በክልሉ የተለያዩ ማዕድናት የሚገኙበትን ቦታ ለመለየት ብዙ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። 

በዚህም መሰረት በክልሉ እስከ አሁን ለኢንዱስትሪ ግብዓት፤ ለጌጣጌጥ እና ብረታብረት ምርት የሚውሉ 76 አይነት ማዕድናት መለየታቸውን ገልጸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹን ወደ ምርት በማስገባት ለኢንዱስትሪ ግብዓት እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም