ቀጥታ፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተገኙ ስኬቶችን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ በትኩረት ይሰራል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ ድሎችን ይበልጥ የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ገለጹ።

የኢዜአ የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሀገራዊ ለውጡ የተበሰረበትን መጋቢት-24 አስመልክቶ ’’ትናንት ዛሬና ነገ ለኢትየጵያ ልዕልና፤ የለውጡ ፍሬዎችና የነገ ተስፋዎች’’ በሚል መሪ ሃሳብ ተወያይተዋል።


 

ዋና ሥራ አስፈፃሚው በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ ኢዜአ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡትን እመርታዊ ስኬቶች በመዘገብ ተደራሽ አድርጓል።

ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ በገባች ማግስት ያጋጠሟትን ፈተናዎች በመቀልበስ በሁሉም መስኮች ድሎችን ማስመዝገቧን ኢዜአ ትኩረት ሰጥቶ በመዘገብ ለህዝብ መረጃዎችን ማድረሱንም አንስተዋል።

ኢዜአ በሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች የአፍሪካዊያንን መፃኢ ዕድል ጭምር የተሻለ የሚያደርግ ሙያዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሰባት ስኬታማ የለውጥ ዓመታት ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁና ሀገራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ገንቢ ሚና መጫወቱንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህልምና መዳረሻ ፍላጎት ሰፊ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ለዚህም እንደተቋም ብሔራዊ መግባባትን በሚፈጥሩ ሁሉም ዓይነት መስኮች ላይ በትጋት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በክልሎች ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የክልሎች ክላስተር ቡድን መሪ ዮሐንስ ወንድይራድ “ትናንት ዛሬና ነገ ለኢትየጵያ ልዕልና፤ የለውጡ ፍሬዎችና የነገ ተስፋዎች’’ በሚል ርዕስ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሁፍ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት የለውጥ አመታት የሀገርን ብልጽግና መሻት የሚያሳኩ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የኢዜአ ሰራተኞች በሀገራዊ ለውጡ የተወሰደው ተቋማዊ የለውጥ እርምጃም የኢዜአን ተቋማዊ እሴት፣ ርዕይና ተልዕኮ መነሻ በማድረግ የእለት ከእለት ተግባራትን በተገቢው መንገድ ለማከናወን ዕድል እንደፈጠረ ተናግረዋል።


 

የኢትየጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተፈራ በቀለ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ በስኬትና ተግዳሮት የታጀበ ነው ብለዋል።

የሀገራዊ ትርክት ግንባታ ክፍተት ሀገራዊ ለውጡ እንዲወለድ አንዱ ምክንያት ነው ያሉት አቶ ተፈራ በዚህም የለውጡ መንግስት ለአሰባሳቢ ትርክት በሰጠው ትኩረት ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በለውጡ ሂደት አዎንታዊ ሚና ካላቸው የመገናኛ ብዙሃን መካከል ኢዜአ አንዱ በመሆኑ በቀጣይም ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ስኬት ቀጣይነት የተሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም