ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሶስተኛው ዓለም አቀፍ የሀገር በቀል የጤና ምርቶች ፎረም ላይ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አቡዳቢ ዛሬ በተጀመረው ሶስተኛው ዓለም አቀፍ የሀገር በቀል የጤና ምርቶች ፎረም ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች።

ፎረሙ "ሀገር በቀል የማምረት አቅምን ማጎልበቻ ለፍትሃዊ የጤና ክብካቤ ተደራሽነት፣ ለዓለም የጤና ደህንነት እና ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።


 

መድረኩ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አስተናጋጅነትና በዓለም የጤና ድርጅት(WHO) አስተባባሪነት የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።

በጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በፎረሙ እየተሳተፈ ሲሆን የሀገር በቀል የመድሐኒት እና የህክምና መገልገያ ግብዓቶችን አስመልክቶ ሚኒስትሯ ገለጻ አድርገዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ የመድሐኒት እና የህክምና መገልገያ ግብዓቶች ምርት አስመልክቶ እያከናወነች ያለችውን ተግባራት እንዲሁም በዘርፉ በሀገራት፣ በአህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት ሊሰጣቸው በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ መስጠታቸውም ተመላክቷል።

በፎረሙ የዓለም ጤና ድርጅት እና የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች የጤና አጠባበቅ ስርዓቶችንና የኢኮኖሚ አቅምን ለማሻሻል እንዲሁም ዘላቂ የሀገር ውስጥና ክልላዊ ምርቶችን ለማሳደግ ወሳኝ በሆኑ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ላይ ይገኛሉ፡፡

እስከ ሚያዚያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም በሚቆየው በዚህ ፎረም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የጋራ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ልዑክ ከፎረሙ ጎን ለጎን ከሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ውይይት እንደሚያደርግም በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም