ስድስተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ውይይት እና የዘላቂ ልማት ግቦች ፎረም ተጀመረ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 29/2017(ኢዜአ)፦ ስድስተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ውይይት እና የዘላቂ ልማት ግቦች ፎረም ዛሬ በዩጋንዳ ካምፓላ መካሄድ ጀምሯል።

ውይይቱ እየተካሄደ የሚገኘው “ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እርምጃዎችን በፋይናንስ መደገፍ ለአፍሪካ ዘላቂ አረንጓዴ እድገት እና ልማት፤ የፍትህ ጉዳይ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።

በመክፈቻው ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ፣ የህብረቱ አመራሮች፣ የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ አጋሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በአዘርባጃን ባኩ የተካሄደው 29ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 29) የተላለፉ ውሳኔዎች በአፍሪካ ላይ የሚኖራቸውን አንድምታ በተመለከተ ምክክር እንደሚደረግ ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው ያመለክታል።

በኮፕ 29 ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ አስመልክቶ ውሳኔ የተደረሰባቸው ጉዳዮች ለአፍሪካ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ አለመስጠታቸውን የገለጸው ህብረቱ በጉዳዩ ሀገራት ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ ገልጿል።

በብራዚል ቤለም በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) የአፍሪካ የጋራ አቋም ምን መሆን አለበት? በሚለው ጉዳይ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።

እ.አ.አ በ2024 አፍሪካን የተመለከቱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች እና በ2025 በሚኖሩ አጀንዳዎች ላይም ምክክር ይደረጋል።

በአዲስ አበባ በተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚቴ (CAHOSCC ) በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ይገመገማሉ።

የአፍሪካ የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችም ሌላኛው የውይይቱ አጀንዳ ናቸው።

በንጹህ መጠጥ ውሃ እና በማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የዋሽ ፕሮጀክት (WASH) አፈጻጸም ለተሳታፊዎች ቀርቦ ምከረ ሀሳብ ይሰጥበታል።

በስብሰባው የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና የዘላቂ ልማት ግቦችን የተመለከተ የውሳኔ ሀሳብ እንደሚጸድቅ የህብረቱ መረጃ ያመለክታል።

ስድስተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ውይይት እና የዘላቂ ልማት ግቦች ፎረም እስከ ነገ ይቆያል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም