ቀጥታ፡

ለምርት ዘመኑ ወደ ሀገር ውስጥ ከ962 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ማዳበሪያ ተጓጉዟል

አዲስ አበባ፤መጋቢት 29/2017 (ኢዜአ)፦በ2017/18 የምርት ዘመን እስከ አሁን ከ962 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን አስታወቀ።

ለምርት ዘመኑ ግብዓት 55 ሺህ ሜትሪክ ቶን ዳፕ የአፈር ማዳበሪያ የጫነችው "MV DIONISIS " የተሰኘችው 20ኛዋ መርከብ ጅቡቲ ወደብ ደርሳ የማራገፍ ኦፕሬሽን መጀመሯንም ገልጿል።

መንግስት ለ2017/18 የምርት ዘመን ግብዓት የሚሆን 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን (24 ሚሊዮን ኩንታል) የአፈር ማዳበሪያ ገዝቶ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እቅድ ይዟል።

ከተያዘው እቅድ ውስጥ እስከ መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም ከአንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ጅቡቲ ወደብ መድረሱንና ከዚህም ውስጥ ከ962 ሺህ 740 ሜትሪክ ቶን በላይ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙን ባለስልጣኑ ገልጿል።

111 ሺህ 378 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ላይ እንደሚገኝም አመልክቷል።

ወደ ሀገር ውስጥ የተጓጓዙት የማዳበሪያ አይነቶች ዩሪያ እና ዳፕ ናቸው።

ማዳበሪያው በድንበር የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪ እና በባቡር መጓጓዙን የባለስልጣኑ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም