አብን በ3ኛ መደበኛ ጉባኤው ዶክተር በለጠ ሞላን የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ ሰየመ - ኢዜአ አማርኛ
አብን በ3ኛ መደበኛ ጉባኤው ዶክተር በለጠ ሞላን የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ ሰየመ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2017(ኢዜአ)፦ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ/አብን/ 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ዶክተር በለጠ ሞላን የፓርቲው ሊቀመንበር፣ አቶ መልካሙ ጸጋዬን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር በማድረግ ሰይሟል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ ዛሬ መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ 3ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ያካሄደ ሲሆን፤ ጉባኤውን በድምቀት በመጸፈም ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር በለጠ ሞላ ድርጅቱ ከምስረታው ጀምሮ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች፣ የተደረጉ ትግሎችንና የተገኙ ድሎችን አውስተዋል።
ሊቀመንበሩ በመክፈቻ ንግግራቸው ድርጅታቸው የአማራን ህዝብን መዋቅራዊ ጥያቄዎች አንግቦ የፈጠረውን ንቅናቄ እንደ ታላቅ ስኬት ሲያነሱ፤ ከውጭና ከውስጥ የገጠሟቸውን ፈተናዎችም ዘርዝረዋል።
ዶክተር በለጠ በንግግራቸው ከጠቀሷቸው ችግሮች ዋነኛው የሰኔ 15/2011 ዓ.ም ክስተትን ሲሆን፤ የአማራ ህዝብ የትግል አንድነት ላይ ጥቁር ነጥብ የጣለ ነው ብለውታል። ከውስጥ በኩልም አመራሩና አባሉ በመደማመጥ እና መከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ባለማዳበሩ ድርጅቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተፈትኗል ብለዋል።
አያይዘውም ለጉባኤውተኛውና ለመላው የአማራ ልሂቅ ካለፉት ችግሮች በመማር በሀሳብ ልዩነት ማመን፣ በልዩነቶች ዙሪያ በሰለጠነ መንገድ መወያየትና መከራከር፣ ከሁሉም በላይ እርስ በርስ መከባበር እና መደማመጥ ይኖርብናል የሚል መልዕክት አፅንኦት ሰጥተው አስተላልፈዋል።
የሊቀመንበሩ ንግግር ላይ ከተጠቀሱ አበይት ጉዳዮች አንዱ የህወሓት ወረራን ለመመከት ድርጅታቸው ያደረገው ተጋድሎ ታሪካዊነት ነው። ዶክተር በለጠ ህወሓት በአማራ ህዝብ ላይ ያለው ጥላቻ ከገደብ ያለፈ መሆኑን በህዝብ ትግል ከስልጣን ከተወገደ በኋላ በፈጸመው ወረራ ወቅት የተፈጸሙ ግፎችን በማስታወስ ወረራውን ለመቀልበስ ከሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የተደረገውን የተባበረ ትግል ሊለመድ የሚገባው ሲሉ አሞካሽተውታል።
ቀጥለውም ከህወሓት ጋር ሲደረግ የነበረው ጦርነት ፕሪቶሪያ ላይ በተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት ከቆመ በኋላ በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀጥታ ችግር አንስተው፤ በግጭቱ የክልሉ ህዝብ እየደረሰበት ያለውን መከራ ለማስቆም "መንግሥት ይሁን የታጠቁ ወንድሞቻችን ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመስጠት በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው መነጋገር ይገባቸዋል" ሲሉ የሰላም ጥሪም አቅርበዋል።
ከሊቀመንበሩ የመክፈቻ ንግግር በኋላ ጉባዔው የድርጅቱን ሪፖርት አዳምጦ ያጸደቀ ሲሆን፤ በመቀጠልም ለቀጣይ ጊዜ የድርጅቱን የቁጥጥር ኮሚሽን እንዲመሩ ዶክተር አያሌው ታለማን በሰብሳቢነት በመሰየም ለምክትል ሰብሳቢና ለአባላት ሹመት ሰጥቶ የድርጅቱን 40 ቋሚና 5 ተለዋጭ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን አጸድቋል።
ከሰዓት በቀጠለው ጉባኤው ልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ በከፍተኛ ትኩረት ውይይቶች ተካሂደዋል። አዲስ የተመረጠው ምክር ቤት በበኩሉ ዶክተር በለጠ ሞላን ሊቀመንበር፣ አቶ መልካሙ ፀጋዬን ምክትል አድርጎ የሰየመ ሲሆን፤ አጠቃላይ ዘጠኝ አባላት ያሉት የአስፈጻሚ ኮሚቴን አጽድቋል። በዚሁ መሠረት:-
1. ዶክተር በለጠ ሞላ ጌታሁንን ሊቀመንበር
2. አቶ መልካሙ ፀጋዬን ምክትል ሊቀመንበር
3. ረዳት ፕ/ር ዳምጠው ተሰማን የፖለቲካ ጉዳይ
4. አቶ የሱፍ ኢብራሂምን የሕግ ጉዳዮች
5. አቶ ጋሻው መርሻን የህዝብ ግንኙነት
6. አቶ ሀሳቡ ተስፋይን አደረጃጀት
7. አቶ ጥበበ ሰይፈን ጽ/ቤት
8. አቶ ማሩ ጃኔን ስትራቴጂና ስልጠና
9. አቶ አንዷለም አላምረውን የውጭ ግንኙነት አድርጎ የሰየመ ሲሆን፤ ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ከፓርቲው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።