ዘመናዊና ብቃት ያለው ሠራዊት እየተገነባ ነው - ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
ዘመናዊና ብቃት ያለው ሠራዊት እየተገነባ ነው - ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን
አዲስ አበባ፤መጋቢት 28/2017(ኢዜአ):-የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት የሚያስጠብቅ ዘመናዊና ብቃት ያለው ሰራዊት እየተገነባ መሆኑን የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን ገለጹ።
የጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት 10ኛ ዙር ምልምል ወታደሮች እና የ27ኛ የባለሌላ ማዕረግተኛ ሰልጣኞች ምርቃት መርሀ ግብር ተከናውኗል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን፣ የባማና መሰረታዊ ወታደር ስልጠና ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ኩመራ ነገሪ፣ የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ሰለሞን ቦጋለ፣ የጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጡምሲዶ ፊታሞ እና ሌሎችም የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ተገኝተዋል።
የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥የጦላይ የከፍተኛ ባለልዩ ማዕረግተኛ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የመከላከያ ሰራዊት የጀርባ አጥንት የሆኑ የበታች ሹሞችን የሚያፈራ ነው።
ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣን ጥቃት በብቃት በመመከት ዳር ድንበሯ የተከበረና የታፈረች ሀገር ማቆየታቸውን አስታውሰው፥በአሁኑ ወቅት መከላከያ ዘመናዊ ሰራዊት የመገንባት ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የመከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ የሚችሉ ወታደሮች የማፍራት ግዳጁን እንዲወጣ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የመከላከያ ሰራዊት አቅሙን በሰው ኃይል፣ትጥቅና በቴክኖሎጂ በመገንባት ጠንካራና አስተማማኝ ሀይል መገንባቱን ተናግረዋል።
የሰራዊታችንን አቅም ለማጎልበት ያለመታከት የምንሰራው የአገሪቷን ጥቅም ለማስጠበቅ ካለን ፅኑ ፍላጎት የመነጨ ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ይመር፤ የሰራዊቱ የማድረግ አቅምም ከመቼውም ጊዜ በላይ ማደጉን አረጋግጠዋል።
ሰራዊቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ያለውን ዝግጁነት ጠቁመው፥ በተለያዩ የማሰልጠኛ ተቋማት ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት የሰራዊቱን የግዳጅ አፈጻጸም እና ዝግጁነት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።
ለመከላከያ ሰራዊት ግንባታ በተሰጠው ትኩረት ፈርሰው የነበሩ ማሰልጠኛ ተቋማት ስራ መጀመራቸውን አንስተው፥ሰልጣኞችም በተግባርና ንድፈ ሀሳብ ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ገቢራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ሰልጣኞች በሚንቀሳቀሱበት የግዳጅ ቀጣና ሁሉ ህዝባዊነትን ተላብሰውና ሰላም ወዳዱን ህዝብ ከጎናቸው በማሰለፍ ግዳጃቸውን በብቃት እንዲወጡም አሳስበዋል።
የጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጡምሲዶ ፊታሞ በበኩላቸው፥ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ከ40 ዓመታት በላይ በዘለቀው የማሰልጠን ልምዱ ለኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ አለኝታነታቸውን ያረጋገጡ የሰራዊት አባላትን አፍርቷል።
የዛሬ 10ኛ ዙር ምልምል ወታደሮች እና 27ኛ ዙር ባለሌላ ማዕረግተኛ ሰልጣኞች ስልጠናቸውን በተሟላ እውቀትና ክህሎት ያጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም ሰልጣኞች በተግባርና በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን እውቀት ሀገራቸውን ለመጠበቅና የህዝባቸውን ሰላም ለማረጋገጥ እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ምሩቃኑ ህዝባቸውን በእኩልነትና በጀግንነት መጠበቅ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የጦላይ ከፍተኛ የባለሌላ ማዕረግተኛ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የሀገር ዘብ የሰራዊት አባላትን በብቃት ከማሰልጠን ባለፈ ትምህርት ቤት በመገንባት፣ በግብርና ልማት ላይ በመሳተፍ ህዝባዊነቱን እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።