ህብረተሰቡ ደም መለገስን ባህል ሊያደርግ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ ደም መለገስን ባህል ሊያደርግ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ
ጋምቤላ፤መጋቢት 28/2017 (ኢዜአ)፦በክልሉ በደም እጦት ምክንያት ለሕልፈት የሚዳረጉ ወገኖችን ለመታደግ ህብረተሰቡ ደም መለገስን ባህል ሊያደርግ ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
በደምና ህብረ ህዋስ ልገሳ ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ ዛሬ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሯ ወይዘሮ ዓለሚቱ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፥ ለህብረተሰቡ የተሟላ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው።
ይሁን እንጂ ለማህበረሰቡ የተሟላ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው ያልተቋረጠ ጥረት የደም አቅርቦት እጥረት ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን ገልጸዋል።
በደም አቅርቦት ችግር ምክንያት በርካታ ታካሚዎች ከክልሉ ውጪ ወደ ሌሎች አጎራባች ሆስፒታሎች በሪፈር እየተላኩ እንደሚገኙም አንስተዋል።
በመሆኑም በደም እጦት ምክንያት ለህልፈት እየተዳረጉ የሚገኙ ወገኖችን ለመታደግ ህብረተሰቡ ደም መለገስን ባህል ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የዕለቱ የውይይት መድረክ ዓላማም ሁሉም ዜጋ ደም የመለገስ ኃላፊነት እንዳለበት ተገንዝቦ የአጋርነት ሚናውን እንዲወጣ ለማስቻል መሆኑንም ርዕሰ መስተደድሯ ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤናና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ትግስት ታደለ በበኩላቸው፥ በደም እጦት ምክንያት የሚጠፋውን ህይወት ለመታደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህበረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ እንዳሉት፥ መሥሪያ ቤታቸው የደም ባንክ አገልግሎቱን ለማሻሻል የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
እንደ ሀገር ባለፉት ስምንት ወራት ከ333 ሺህ በላይ ዩኒት ደም ለሰብሰብ ታቅዶ ከ278 ሺህ በላይ ደም መሰብሰቡን ጠቁመዋል።
አፈፃፀሙ የተሻለ ቢሆንም አሁንም ብዙ መስራት ይጠበቃል ብለዋል ምክትል ዋና ዳሬክተሩ።
የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አቤል አሰፋ በበኩላቸው፥ ቋሚ ደም ለጋሾችን በማበራከት የደም አቅርቦቱን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም አቅርቦቱና ፍላጎቱን ማጣጣም አልተቻለም ብለዋል።
በመሆኑም እያጋጠመ ያለውን የደም አቅርቦት ችግር ለማቃለል የሁሉም ህብረተሰብ ድጋፍና ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤትና ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በደምና ህብረ-ህዋስ ልገሳ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የክልሉን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
በዕለቱ የደም ልገሳ መረሃ ግብርም ተካሂዷል።