የታላቁ ሩጫ ጅማ የከተማዋን የቱሪስት መስህቦች ለማስተዋወቅና ስፖርቱንም ለማነቃቃት ትልቅ ሚና ይኖረዋል-ተሳታፊዎች

ጅማ፣መጋቢት 28/2017(ኢዜአ)፦የታላቁ እሩጫ ጅማ 2017 የጅማን የቱሪስት መስህቦችን ለማስተዋወቅና ስፖርቱንም ለማነቃቃት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ሲሉ የውድድሩ ተሳታፊዎች ገለጹ።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት "ታላቁ ሩጫ ጅማ 2017" የጎዳና ላይ ሩጫ መርሃ ግብር በጅማ ከተማ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎችን በማሳተፍ ዛሬ ተካሄዷል።

መርሃ ግብሩ የጅማን የቱሪስት መስህቦችና የጅማን የቡና ልማት አቅም ማስተዋወቅ ዓላማ ያደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን አብሮነትና ወንድማማችነትን ለማጠናከርም ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው ተጠቅሷል።

የሩጫው ተሳታፊዎች እንዳሉት መርሃግብሩ የጅማን የቱሪስት መስህቦች ለማስተዋወቅና ስፖርቱንም ለማነቃቃት ያግዛል።

ከሩጫው ተሳታፊዎች መካከል አቶ ታሪኩ በላቸው፥ለጤና በተደረገው ውድድር ላይ መሳተፉቸውን ገልጸው፤ መርሃ ግብሩ ጅማ ያላትን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብት ለማስተዋወቅ ይረዳል ብለዋል።

ይህ ዓይነቱ በጎ ልማድ ቢዘወተር በርካታ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ስለሚኖረው ከዚህ በበለጠ በትኩረት ሊሰራበት ይገባዋልም ብለዋል።

ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሪት ምህረት ሀሰን ይህ የውድድር መርሃግብር ወጣቱንም ጎልማሳውንም ለስፖርት የሚያነሳሳ እና አዝናኝ መሆኑን ገልጻለች።

ከሩጫውም በተጨማሪ የተለያዩ ትዕይንቶችን ያካተተ በመሆኑና በርካታ ሰዎች የሚሳተፉበት አዝናኝ መሆኑን ተናግራለች።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ በበኩላቸው፥ የሩጫው ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ በየአካባቢው ያሉ የቱሪስት መስህቦችን እና ባህላዊ እሴቶችን በማስተዋወቅ ቱሪዝምን ከመደገፍ ባለፈ ስፖርታዊ ተነሳሸነትን መፍጠር ነው ብለዋል።

ውድድሩ የአዋቂዎች የ15 ኪ.ሜ እና የህጻናት የአምስት ኪ.ሜ ውድድር ያካተተ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህ የታላቁ ሩጫ ጅማ 2017 መርሃግብር ውድድር ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡት ተወዳዳሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም