ቀጥታ፡

196ኛው የማንችስተር ደርቢ 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2017(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ31ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ማንችስተር ዩናይትድ እና ማንችስተር ሲቲ ዛሬ የሚያደርጉት የደርቢ ፍልሚያ ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች  ጨዋታ ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ላይ በኦልድትራፎርድ ስታዲየም ይካሄዳል።

ማንችስተር ዩናይትድ በ37 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማንችስተር ሲቲ በ51 ነጥብ 5ኛ ደረጃን ይዟል። 

ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የአሁኑ ለ196ኛ ጊዜ ነው። 

ቡድኖቹ ከዚህ በፊት ባደረጓቸው 195 ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ 80 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ማንችስተር ሲቲ 61 ጊዜ ሲያሸንፍ 54 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።

ማንችስተር ዩናይትድ እና ማንችስተር ሲቲ የአንድ ከተማ ባላንጣ ቡድኖች ናቸው። 

ክለቦቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ1881 ነበር። በዚህ ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ 3 ለ 0 አሸንፏል።

ቡድኖቹ ከመጀመሪያ ጨዋታቸው አንስቶ ለ144 ዓመታት የቆየ ፉክክር በእንግሊዝ እና በአውሮፓ መድረክ አድርገዋል።

ማንችስተር ዩናይትድ የሊጉን ዋንጫ 20 ጊዜ በማንሳት የበላይነቱን ይዟል።  ማንችስተር ሲቲ 10 ጊዜ የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል። 

የ35 ዓመቱ እንግሊዛዊ ጆን ብሩክስ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራሉ።

በሌላ በኩል የሊጉ መሪ  ሊቨርፑል ወደ ምዕራብ ለንደን በማቅናት ከፋልሃም ጋር ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም