በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪዝም መደራሻ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅ እየተሰራ ነው - የቱሪዝም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪዝም መደራሻ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅ እየተሰራ ነው - የቱሪዝም ሚኒስቴር
ጅማ፤ መጋቢት 27/2017 (ኢዜአ)፦ የቱሪዝም ሚኒስቴር በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪዝም መደራሻ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የ2017 ታላቁ የጅማ ሩጫ ነገ በጅማ ከተማ ይካሄዳል።
ነገ የሚካሄደውን የታላቁ ሩጫ መርሃ ግብር አስመልክቶ የቱሪዝም ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት መግለጫ ተሰጥቷል።
በቱሪዝም ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ግዛው፤ ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ ቅርሶችና በባህላዊ እሴቶች የታደለች ሀገር መሆኗን አስታውሰዋል።
በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪዝም መዳራሻ ስፍራዎችን በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ጅማ አካባቢ በቡና ምርት በስፋት የሚታወቅ እና አካባቢው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቡና ወዳጅ ተጓዦች ተመራጭ መዳረሻ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
ነገ የሚካሄደው የ2017 ጅማ ታላቁ ሩጫ የቱሪዝም ዘርፉን ከስፖርት ጋር አስተሳስሮ ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር በበኩላቸው ጅማ ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ መሆኗን አንስተው ነገ የሚካሄደው ሩጫም መልካም አጋጣሚ መሆኑን አመልክተዋል።
መርሃ ግብሩ ስፖርትና ቱሪዝምን ያዋሀደ እንደመሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው 2017 የጅማ ታላቁ ሩጫ ለከተማው ብዙ እድሎች ይዞ የሚመጣ ነውም ብለዋል።