በኢትዮጵያ ለቆዩና እየተንከባለሉ ለመጡ ችግሮች ሁነኛ መፍትሄው በመመካከር ዘላቂ መፍትሄ መሻት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለቆዩና እየተንከባለሉ ለመጡ ችግሮች ሁነኛ መፍትሄው በመመካከር ዘላቂ መፍትሄ መሻት ነው
ባህር ዳር፤ መጋቢት 27/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ለቆዩና እየተንከባለሉ ለመጡ ችግሮች ሁነኛ መፍትሄው በመመካከር ዘላቂ መፍትሄ መሻት መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ(ዶ/ር) ገለጹ።
በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች የማህበረሰብ ወኪሎች በተገኙበት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ከ267 ወረዳዎች የተወከሉ ከ4 ሺህ 500 በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ይሳተፋሉ።
በባህር ዳር ከተማ በተከናወነው የማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ(ዶ/ር)፤ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በመተማመን ላይ የተመሰረተ ጥልቅ ምክክር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረው ከዚህ ቀደም በ10 ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት በተሳካ መልኩ መከናወኑን ተናግረዋል።
በአማራ ክልልም ምክክሩ በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል።
በመሆኑም ተነጋግሮ በመግባባትና በመተማመን እንዲሁም ለምክክር ቅድሚያ በመስጠት ችግሮችን ለመፍታት እንዘጋጅ ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለቆዩና እየተንከባለሉ ለመጡ ችግሮች ሁነኛ መፍትሄው በመመካከር ዘላቂ መፍትሄ መሻት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው፤ ኢትዮጵያን ሊያድናት የሚችለውና ትክክለኛው አማራጭ ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ ምክክር መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በምክክር ተግባብቶ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሁላችንም ልንዘጋጅ ይገባል ብለዋል።
የጥፋት መንገዶችን በመተው ችግሮችን ተነጋግሮ የመፍታት ባህል ማዳበር እንደሚገባም አንስተዋል።
ምክክሩ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ታሳቢ ተደርጎ እየተከናወነ ነው ያሉት ደግሞ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) ናቸው።
እንዲሁም ችግሮች በሚፈጠሩበት ወቅት በመነጋገር የመፍታት ባህል እንዲዳብርም ጭምር እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በምክክር ሂደቱ የሁሉም ማህበረሰብ ሃሳብ በአጀንዳነት እንዲካተት ሰፊ ስራ መሰራቱንና እስካሁን የተሰራው ስራም ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽነር አምባሳደር መሃሙድ ድሪር በበኩላቸው ችግሮችን ለመፍታት መመካከርና መነጋገር ግድ ይላል ብለዋል።
በመሆኑም በምክክርና በውይይት ችግሮችን ለመፍታት በመተማመን ለመጣችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል በማለት የኢትዮጵያ ችግር በራሷ ልጆች የሚፈታ መሆኑን አስገንዝበዋል።