በክልሉ ተኪ ምርቶችን በስፋትና በጥራት በማምረት የውጭ ምንዛሪን ለማዳን በቅንጅት እንሰራለን - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ተኪ ምርቶችን በስፋትና በጥራት በማምረት የውጭ ምንዛሪን ለማዳን በቅንጅት እንሰራለን - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
አርባምንጭ፤ መጋቢት 27/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተኪ ምርቶችን በስፋትና በጥራት በማምረት የውጭ ምንዛሪን ለማዳን ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
በክልሉ "ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ጥላሁን ከበደ ተኪ ምርቶችን በስፋትና በጥራት በማምረት የውጭ ምንዛሪን ለማዳን ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በቅንጅት ይሠራል ብለዋል።
ለውጡ ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ተግባራዊ የተደረገው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እንዲመዘገብ የላቀ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸው ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ዘርፉ የነበረበትን ማነቆ ለመፍታት እንደ መንግስት የተወሰዱ ቁርጠኛ እርምጃዎች እያስመዘገቡት ያለውን ውጤት የበለጠ ለማላቅ አምራች ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትኩረት አቅጣጫን ተከትሎ የመደገፍ ስራ ይሰራል ብለዋል።
ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የመስሪያ፣ የማምረቻ እና የመሸጫ ቦታዎችን በማመቻቸት እንዲሁም የፋይናንስና የገበያ ትስስር ችግሮች እንዲፈቱ ከዘርፉ አካላት ጋር በመነጋገርና በመወያየት መፍትሄ እያስቀመጥን እንሄዳለን ሲሉም ገልጸዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪውን ሚና በማላቅ ሀገር በቀል ሀብቶችን ጥቅም ላይ በማዋል የውጭ ምንዛሪን በማዳን የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ ርብርብ እናደርጋለን ነው ያሉት።
የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ቦጋለ ቦሼ(ዶ/ር) አምራች ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን ገልጸዋል።
ክልሉ ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት የአምራች ኢንዱስትሪውን የፋይናንስ፣ የገበያና የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ተቋማዊ አደረጃጀትን በማጠናከርና የኢትዮጵያ ታምርት ስትሪንግ ኮሚቴ በማዋቀር ሰፊ ተግባር እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
አምራች ኢንዱስትሪውን በጥናትና በምርምር ለመደገፍ በክልሉ ከሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመልማት አቅም ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንና በዚህም የኢንዱስትሪ አቅም ልየታና አዋጭነት ጥናት ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ የክልሉ ኢንዱስትሪ ቢሮ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ላይ በተከናወኑ ተግባራትና ተግዳሮቶች ዙሪያ ሰነድ የቀረበ ሲሆን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የአምራች ኢንዱስትሪ ዕድሎችና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።