ቀጥታ፡

ቴክኖሎጂን በመጠቀም ግልጽና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2017 (ኢዜአ)፦ የቴክኖሎጂ ሥርዓትን በመጠቀም ግልጽና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባችውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ገለጹ።

በፍርድ ቤቶች የአሰራር መዋቅርና የዲጂታል ሥርዓት ላይ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚመክረው ሀገር አቀፉ የሕግ ተርጓሚዎች የምክክር መድረክ በቢሸፍቱ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፥ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት መወሰኛ አዋጅ 1231/2013 አንቀጽ 25/1/ መሰረት ተከታታይ የጋራ መድረክ በየስድስት ወሩ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።


 

መድረኩም የጋራ ግንኙነትን ወደ ተሻለ ደረጃ በማሸጋገር የዳኝነት ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ተደራሽ፣ ቀልጣፋና የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም የቴክኖሎጂ ሥርዓትን በመጠቀም ግልጽና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ተስፋ ሰጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

የዳኝነት አገልግሎቱም በተቀናጀ የጋራ ስልት መሬት ላይ ያለውን እውነት በሚያረጋግጥ መልኩ በክልሎች መካከል የሐብት ብክነትን ማዳን የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሥርዓት መዘርጋቱን አስረድተዋል።

የፍርድ ቤቶች የቴክኖሎጂ የአሰራር ሥርዓቶች ተናባቢ፣ ተመጋጋቢና ለሁኔታዎች ተለዋዋጭ የማገልገል አቅም እንዲሆኑ በማስቻል የተገልጋዩን እርካታ በሚያረጋግጥ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

መድረኩም የሕግ የበላይነትና ፍትሕዊነትን ማረጋገጥ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር አፈፃጸማናቸውን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

በዳኝነት ዘርፍ የሚፈለገውን እርካታ ለማምጣት ፍርድ ቤቶች ግባቸውን ለማሳካት ሙሉ የሆነ ቁመና ሊኖራቸው ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም