ቀጥታ፡

ከውጭ በሚገቡ የእንስሳት መድሀኒትና የህክምና መሳሪያዎችን ጥራት ለማስጠበቅ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው - ባለስልጣኑ

አዳማ፤ መጋቢት 27/2017 (ኢዜአ)፦ ከውጭ በሚገቡ የእንስሳት መድሀኒትና የህክምና መሳሪያዎችን ጥራት ለማስጠበቅ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን አስታወቀ።

የእንስሳት መድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ክትትልና ቁጥጥር አሰራር ለማሳለጥ በተዘጋጀው መመሪያ ላይ በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የእንስሳት ሬጉላቶሪ ዘርፍ ዳይሬክተር ዶክተር ሃሚድ ጀማል፤ የእንስሳት መድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ጥራትን ለማስጠበቅ የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።


 

ለተግባራዊነቱም የምዝገባ፣ የናሙና ምርመራ ጥራት ማረጋገጥ ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህን ለማስፈጸም በእንስሳት መድሀኒት ምርትና የግብዓት አቅርቦት ላይ የተዘጋጁ መመሪያዎች ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአሁኑ የምክክር መድረክም የመመሪያ ማስፈፀሚያ የአሰራር ማኑዋሎች ተዘጋጅተው በባለድርሻ አካላት ግብዓት ለማደበር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ከውጭ በሚገቡ የእንስሳት መድሀኒትና የህክምና መሳሪያዎችን ጥራት ለማስጠበቅ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛልም ነው ያሉት።


 

በባለስልጣኑ የእንስሳት መድሀኒት ቁጥጥር መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሰለሞን ከበደ፤ የተቋሙ የቁጥጥርና ክትትል ስራዎች የዲጂታል አሰራርን በተከተለ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የእንስሳት መድሀኒትና ህክምና መሳሪያዎች ምዝገባ መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን መመሪያውን ማስፈፀም የሚያስችሉ የአሰራርና የህግ ማዕቀፎች ስለመዘጋጀታቸውም አንስተዋል።

የእንስሳት መድሀኒት አጠቃቀም፣ የአቅርቦት አማራጮችን ለማስፋትና ሊታዘዙ የሚችሉ መድሀኒቶች በምዝገባና ያለምዝገባ እንዲታዘዙ የሚያስችሉ መዘርዝሮች ጭምር ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

የእንስሳት መድሀኒቶች ጥራትና ደህንነታቸው የተጠበቁ ሆነው እንዲገቡና ክትባቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ከመድሀኒት አምራቾችና አቅራቢዎች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም