በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተደረገልን ድጋፍ የተሻለ ህይወት እንድንመራ አድርጎናል- ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተደረገልን ድጋፍ የተሻለ ህይወት እንድንመራ አድርጎናል- ተጠቃሚዎች
ወልዲያ፤ መጋቢት 26/2017(ኢዜአ)፡- በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተደረገልን ድጋፍ በፊት የነበርንበትን አኗኗር በመቀየር አዲስ ህይወት እንድንመራ አስችሎናል ሲሉ በሰሜን ወሎ ዞን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ገለጹ።
በያዝነው በጋ ከ152 ሺህ በላይ ወጣቶችን በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሰማራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታውቋል።
በዞኑ ጋዞ ወረዳ 01 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ የሺ ሲሳይ ለኢዜአ እንደገለጹት አቅም የሌላቸው በመሆኑ አራት ቤተሰባቸውን ይዘው በፈራረሰ ቤት መኖር ከጀመሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል።
በዚህም በበጋ በጸሃይና ንፋስ፣ በክረምት ደግሞ በዝናብና ቁር ሲሰቃዩ እንደነበር ጠቁመው አሁን ላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የፈረሰ ቤታቸውን ስለሰሩላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በወጣት ወገኖቼ እርዳታና ድጋፍ ህጻናት ልጆቼ አዲስ በተሰራ ቤት ለመኖር በመብቃታቸው ደስታዬ ወሰን የለውም፤ ድጋፉን ላደረጉልኝ ሁሉ ፈጣሪ ይጠብቅልኝ ብለዋል።
"በወጣቶች አነሳሽነት ቤቴ እንደገና በመታደሱ አዲስ ህይወት መኖር እንድጀምር አስችሎኛል" ያሉት ደግሞ በዚሁ ወረዳ የ07 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አባይ ባዬ ናቸው።
"የፈረሰ ቤቴን በፀሃይ ወቅት ጣሪያውን ቅጠል እያለበስኩ፤ በዝናብ ወቅት ደግሞ ፍሳሹን በባልዲ እየገደብኩ እኖር ነበር" ያሉት ወይዘሮ አባይ ''አዲስ ቤት ሰርተው ላስረከቡኝ ወጣቶች እድሜና ጤና ይስጥልኝ'' ብለዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የወጣቶች ማካተት፣ ንቅናቄና ተሳትፎ ቡድን መሪ ወይዘሮ ትዕግሥት ሞገስ በበኩላቸው 152 ሺህ 172 ወጣቶች በበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰማራታቸውን ገልፀዋል።
ወጣቶቹ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገንና በመገንባት፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች 14 ተግባራት ላይ በመሰማራት የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየፈቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ካከናወኑት ተግባራት ውስጥም የ29 አቅመ ደካሞችን ቤት በአዲስ በመስራትና በመጠገን ያበረከቱት አስተዋጽኦ አርዓያነት ያለው ተግባር ነው ብለዋል።
ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በማሰባሰብ 161 ታማሚዎችን በማሳከም፣ 82 ዩኒት ደም በመለገስ፣ የ52 ትምህርት ቤቶችን ወንበርና ጠረጴዛዎችን መጠገንና ሌሎች ድጋፎችን ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
በግብርናው ዘርፍም የመስኖ ካናሎችን በመጥረግ፣ በአፈርና ውሃ እቀባ ስራ በመሰማራትና በመስኖ ልማቱ ደካማ አርሶ አደሮችን በማገዝ ምርታማ እንዲሆኑም አስችለዋል ብለዋል።
እስከ ሰኔ 30/2017 ድረስ በሚቀጥለው የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎትም ከ400 ሺህ በላይ ወገኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።