የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በሩሲያ ማስተዋወቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በሩሲያ ማስተዋወቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2017 (ኢዜአ)፦ በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመ (ዶ/ር) የሩሲያ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤትን የጎበኙ ሲሆን ከምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፕላቶኖቭና ከሌሎች የምክር ቤቱ አመራሮች ጋር በሞስኮ ተወያይተዋል።
አምባሳደር ገነት በኢትዮጵያ ስላለው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በተለይም በግብርና፣ ፋርማሲዩቲካል፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን ኤና ሌሎች አማራጮችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
መንግስት በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ መሰማራት ለሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በሩሲያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ምክር ቤቱ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በሩሲያ በጋራ የሚያስተዋውቁበት ሁኔታ እንዲፈጥርም ጠይቀዋል።
የሩሲያ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፕላቶኖቭ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በትብብር ሊሰሩባቸው የሚችሉ ሰፊ አማራጮች እንዳላቸው ገልጸዋል።
የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) መሰረተ ልማት፣ ዲጂታላይዜሽን፣ ትምህርት፣ ዘላቂ የከተማ ልማት እና የስማርት ሲቲ ግንባታ ከትብብር መስኮቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
ሁለቱ ወገኖች በምክር ቤቱ እና በአፍሪካ እና ሩሲያ የኢኮኖሚ ትብብር ማስተባበሪያ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት (አፍሮኮም) አማካኝነት የንግድ እድሎችን በጋራ ለማስተዋወቅ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን በሞስኮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።