ቀጥታ፡

የኢትዮጵያንና የኡጋንዳን ዘርፈ ብዙ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንሰራለን-ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን እና የኡጋንዳን የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንሰራለን ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።

አራተኛው የኢትዮጵያ እና የኡጋንዳ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ተካሒዷል፡፡

በሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ የሁለቱ አገራት ትብብር ያለበት ደረጃ ተገምግሞ የቀጣይ የትብብር መስኮች ተለይተዋል፡፡

ከስብሰባው በኋላ ሁለቱ አገራት በቀጣይ ትብብር በሚያደረርጉባቸው ዘርፎች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፣ የኢትዮጵያ እና የኡጋንዳ ትብብር ዘመናትን የተሻገረ መሆኑን ገልጸዋል።

በጋራ ኮሚሽን ስብሰባው በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የትብብር ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

ሀገራቱ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች ትብብርን የሚያጠናክር ስምምነት መፈራረማቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር ገልጸው፤ የትብብር ስምምነቱ ግቡን እንዲመታ ኢትዮጵያ አበክራ ትሰራለች ብለዋል፡፡

የኡጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦዶንጎ ጄጄ አቡበክር በበኩላቸው፤ የኡጋንዳ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በህዝብ ለህዝብ የተሳሰረ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው ያረጋገጡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም