በአቡዳቢ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ ባልደረቦች ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የ26 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
በአቡዳቢ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ ባልደረቦች ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የ26 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2017(ኢዜአ)፦ በአቡዳቢ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ ባልደረቦች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቂያ የድጋፍ ንቅናቄን በመቀላቀል የ26 ሺህ ዶላር ቦንድ ግዢ ፈጽመዋል።
በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዑመር ሁሴን(ዶ/ር) ድጋፋን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም የቦንድ ግዢው የተከናወነው መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም 14ኛ ዓመቱን የያዘው የአፍሪካ ግዙፉ ግድብ በጥቂት ወራት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ መንግስት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ባለበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል።
የኤምባሲው ባልደረቦችም የግድቡ ግንባታ ማጠናቀቂያ ንቅናቄን በመቀላቀል ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በተጨማሪም በአቡዳቢ እና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በግድቡ ማጠናቀቂያ ንቅናቄ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችል ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
በሰባቱም ኤምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በጎ ምላሽ በመስጠት እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ከሀገራቸው ጎን እንዲቆሙም አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡