የኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ባለሙያዎች ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው- ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ባለሙያዎች ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው- ሂሩት ካሳው (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣መጋቢት 26/2017 (ኢዜአ)፦የኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ባለሙያዎች ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ከተማ የባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ "ኢትዮጵያ ችላለች" በሚል መር ሃሳብ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ልዩ የኪነ ጥበብ ንቅናቄ መድረክ አስጀምሯል።
የቢሮው ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የይቻላል መንፈስ ያጠናከረ ስንቅ ነው።
ቢሮው ከዚህ ቀደም የዘርፉ ተዋንያን ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የማስተባበር ሥራ ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።
ዛሬ የተጀመረው ንቅናቄ የዘርፉ ተዋንያን በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ለሚገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያን በተለያየ መልኩ ያደረጉት ድጋፍ የግድቡ ግንባታ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ አድርሶታል ብለዋል።
አሁን የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አመልክተው፤ እያንዳንዱ ዜጋ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ እንደተናገሩት፤ ማህበሩ ለግድቡ ግንባታ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል። በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥላል።
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ዳዊት ይፍሩ በበኩላቸው፤ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በገንዘብም ሆነ በዓይነት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ሆቴሎች ማህበር ፕሬዚዳንት አስቴር ሰለሞን እንደተናገሩት፤ የሆቴል ባለቤቶች ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው።