በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሬትን ለማከም የሚደረጉ ጥረቶች ውጤታማ እየሆኑ ነው - የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሬትን ለማከም የሚደረጉ ጥረቶች ውጤታማ እየሆኑ ነው - የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት
አዳማ፤መጋቢት 26/2017(ኢዜአ)፦ በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሬትን ለማከም ኖራን ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያና ቨርሚ ኮምፖስት ጋር በመደባለቅ ጥቅም ላይ በማዋል ውጤት እየተገኘ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በኢንስቲትዩቱ የተዘጋጀ የአፈር አሲዳማነትን በዘላቂነት ለመከላከል የተዘጋጀ ሀገራዊ የባለድርሻ አካላት ምክክር በአዳማ እየተካሄደ ነው።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአፈርና ውሃ ምርምር ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ(ዶ/ር) በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት የአፈር አሲዳማነት ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ስራዎች ተሰርቷል።
በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሬትን ለማከም ኖራን ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያና ቨርሚ ኮምፖስት ጋር በመደባለቅ ጥቅም ላይ በማዋል ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።
እንዲሁም በክልሎች የግብርና ምርምር ተቋማትና በኢንስቲትዩቱ የአፈር አሲዳማነትን የሚቋቋሙ 10 የሰብል ዝርያዎች ፈልቀው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርጓልም ብለዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም በአፈር አሲዳማነት ተጠቅተው ምርት ማምረት ያቆሙ መሬቶችን ደግሞ ለቡናና ሻይቅጠል ልማት እንዲውሉ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ባለፉት አመታት በተለያዩ አካባቢዎች በተበታተነ መልኩ የአፈር አሲዳማነትን የማከም ሙከራ ሲደረግ መቆየቱን አውስተው አሁን ላይ 228 ሙከራዎችን በማቀናጀት ለውጤት መብቃቱን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ድሪባ ገለቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሀገሪቱ ከሚታረሰው መሬት ውስጥ 43 በመቶ በአሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን ለመድረኩ ማቅረቡን ጠቅሰው ተጨማሪ ግብዓት በማዳበር ለምርምር ተቋማት፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለማጋራት ይሰራል ብለዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል አለሙ በሰጡት አስተያየት የአፈር አሲዳማነት በክልሉ በስፋት እንዳለ ጠቅሰዋል።
በዚህም በክልሉ ከሚታረሰው መሬት ውስጥ ከ8 ሺህ ሄክታር በላይ በአሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን የሚፈቱ ምርምሮች እየተካሄዱ ሲሆን የኖራ ክምችት ከመለየት ጀምሮ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።