ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ254 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ፤መጋቢት 26/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ254 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የተቋሙ ቃል አቀባይ ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ቸኮል ገለጹ።

ረዳት ኮሚሽነሩ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አመራርና አባላት ከ14 ዓመት የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል።


 

የፖሊስ አባላቱ ለግድቡ ደህንነት የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ስራው እንዳይቋረጥ ጥበቃ በማድረግ የላቀ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።

አመራርና አባላቱ የግድቡን ደህንነት ከመጠበቅ ባሻገር በኢትዮጵያዊነታቸው የዜግነት ኃላፊነትን በመወጣት የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በዚህም በአጠቃላይ ከ254 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ከፌደራል ፖሊስ መደረጉን ነው ቃል አቀባዩ የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለግድቡ ሁለንተናዊ ደህንነት በመጠበቅ እና በገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም