ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውስጥ አቅምን በማጠናከር ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መፈጸም እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውስጥ አቅምን በማጠናከር ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መፈጸም እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው
ድሬደዋ፤ መጋቢት 26/2017(ኢዜአ) ፡-ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የውስጥ አቅምን በማጠናከር ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መፈጸም እንደሚቻል ያረጋገጠ መሆኑ ተገለጸ።
የድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ለህዳሴ ግድብ የሚደረገውን ህዝባዊ ድጋፍ የሚያጠናክር ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እንደተናገሩት፤ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በህብረት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን የመፈጸም አቅም እንዳላቸው ያረጋገጡበት ነው።
ፕሮጀክቱ ትውልድ ተሻጋሪ ግዙፍ ሃብት መሆኑን የገለፁት ምክትል ከንቲባው "ኢትዮጵያዊያን ወረራን መመከት ብቻ ሳይሆን የትኛውንም አገራዊ ጉዳይ በመተባበር መፈጸም እንደሚቻል ያሳየንበት ደማቅ ታሪካችን ነው" ብለዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አሰፋ በበኩላቸው የድሬደዋ ነዋሪዎች፣ ሠራተኞች፣ ተቋማት እና ባለሃብቶች የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት እስካሁን ከ103 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
ግድቡ የይቻላል መንፈስን ያሰረፀ ዘመን ተሻጋሪ በመሆኑ አሁንም ዳር እንዲደርስ ህብረተሰቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ እና ሠራተኞች ለህዳሴው ግድብ ዳር መድረስ በገንዘብ እና በዕውቀት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርስቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ተማም አውል (ዶ/ር) ናቸው።
በእስካሁኑ ዩኒቨርሲቲውና ሠራተኞች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የድሬደዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላት፣ በብልፅግና ፓርቲ የድሬደዋ አስተዳደር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እና አመራሮች እንዲሁም የዩኒቨርስቲው አመራሮች፣ መምህራንና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።