ቀጥታ፡

አምባሳደር ጀማል በከር ከራውልፒንዲ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ልዑክ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2017(ኢዜአ)፡- በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር በራውልፒንዲ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኡስማን ሻውካት ከተመራ ልዑክ ጋር ዛሬ በኢስላማባድ ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ የኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው አማራጮች ላይ ትኩረቱን በማድረግ መካሄዱን በኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

አምባሳደር ጀማል ለምክር ቤቱ ልዑክ ስለ ኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት እድሎች ገለጻ አድርገዋል ።

የኢትዮጵያ መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ባለፉት 7 ዓመታት በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ህግ እና ማህበራዊ መስኮች ያደረጋቸውን ማሻሻያዎች በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና ዓለም አቀፍ ንግድ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አመልክተዋል።

የራውልፒንዲ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኡስማን ሻውካት ምክር ቤቱ ከኢትዮጵያ አቻ ተቋም ጋር ትስስር የመፍጠር ፍላጎት እንዳለው አመልክተዋል።

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ መግለጻቸውን በኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የራውልፒንዲ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት እ.አ.አ በ1952 የተቋቋመ ሲሆን በርካታ የፓኪስታን አምራች ኩባንያዎች እና የንግድ ተቋማትን አቅፎ የያዘ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም