የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተልዕኮውን በአስተማማኝ ሁኔታ የተወጣና የሀገር ህልውናንም በጀግንነቱ ያፀና ነው -ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተልዕኮውን በአስተማማኝ ሁኔታ የተወጣና የሀገር ህልውናንም በጀግንነቱ ያፀና ነው -ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተልዕኮውን በአስተማማኝ ሁኔታ የተወጣና የሀገር ህልውናንም በጀግንነቱ ያፀና ነው ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
ዋና አዛዡ በአቪዬሽን ሙያ ተቋሙን ለማገልገል ወደ አየር ኃይል አካዳሚ ለስልጠና የተቀላቀሉ ምልምል የሰራዊት አባላትን በአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተጣለበትን ተልዕኮ በአስተማማኝ ሁኔታ በመወጣት የሀገር ህልውናንም በጀግንነቱ ያፀና ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ በዚህ ሁሉ የታሪክ ጉዞ ውስጥ ከራሳቸው ይልቅ ሀገር ያስቀደሙና ለኢትዮጵያ ክብር ሲሉ የተዋደቁ ታላላቅ ጀግኖችን ያፈራ መሆኑን መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሰልጣኞቹ ተልዕኳቸውን በፅኑ ሊረዱ እንደሚገባ ያስታወቁት ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በቀጣይም ከወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት እስከ አየር ኃይል አካዳሚ ድረስ በተዋረድ የሚሰጡትን ስልጠናዎች በብቃት ለማጠናቀቅ ራሳቸውን በስነ ልቦና ብሎም በአካል እና አእምሮ ብቁ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በዕለቱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች መስፈርቱን ያሟሉ ሰልጣኞችን መልምሎ በአቪዬሽን ሙያ ዘርፍ ወደፊት ተቋሙን እንዲያገለግሉ በተያዘው እቅድ መሠረት ለማሰልጠን ወደ አካዳሚው ያስገባ መሆኑም ተገልጿል።