ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው በንግግር ብቻ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው በንግግር ብቻ ነው
ሚዛን አማን፤ መጋቢት 26/2017(ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው በንግግር ብቻ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰሎሞን አየለ ገለጹ።
በሚዲያና በሌሎች አማራጮች የሀገርን ጥቅም የሚጎዱና ልማትን የሚያደናቅፉ እንቅስቃሴዎች መሳተፍና ተባባሪ ሆኖ መቆም በፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ተናግረዋል።
በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮችና የፖለቲካ እንቅስቃሴውን በተመለከተ ኢዜአ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰሎሞን አየለ እና ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ጋር ቆይታ አድርጓል።
የሀገር ብሄራዊ ጥቅም፣ የህዝብ ሰላም፣ የልማትና ህብረ ብሄራዊ አንድነት ጉዳይ የሀገር ህልውና መሰረቶች መሆናቸውን ያነሱት ሰብሳቢው ለዚህም ያለ ልዩነት መቆም ግድ መሆኑን ይናገራሉ።
የማያግባቡ ጉዳዮችን ተነጋግሮ መፍታት ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን አንስተው ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም ንግግር ብቸኛው መንገድ መሆኑን አለበት ብለዋል።
ከዚህ ውጭ የሀገርን ጥቅም የሚጎዱና ልማትን የሚያደናቅፉ እንቅስቃሴዎች ላይ ተባባሪና ተሳታፊ መሆን በፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ተናግረዋል።
የጋራ ቤታችን የሆነችው ኢትዮጵያ ለሰላሟና ለእድገቷ በጋራ መቆም ይገባናል ብለዋል።
በዚህ ረገድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሀሳብ ልዩነት ውስጥ በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም በመያዝ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኅብረት ፓርቲ አመራሮች መካከል አቶ ወንድሙ ገዛኸኝ፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ አሳታፊና ምቹ የፖለቲካ ምህዳር የተፈጠረ በመሆኑ በሰላማዊ ትግል አሸናፊ መሆን እንደሚቻል ተናግረዋል።
በዚህ ዘመን ከመነጋገር በስተቀር የጥፋት መንገዶችን መከተል በፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ገልጸዋል።
የካፋ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ፓርቲ አመራር አቶ ክፍሌ መሸሻ፤ ለሰላምና ልማት እንዲሁም ለአብሮነት የማይጠቅሙ ከፋፋይ ሀሳቦችን በጋራ መታገል ይገባል ብለዋል።
የሃሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም በሀገርና በህዝብ ሰላምና ልማት ማንም ቢሆን በተቃርኖ መቆም የለበትም ሲሉም ተናግረዋል።