ቀጥታ፡

በክልሉ የተገኘውን ሰላም በማጽናት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ስኬታማ ለማድረግ በትብብር ይሰራል

ጋምቤላ፤ መጋቢት 26/2017(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል የተገኘውን ሰላም በማጽናት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ስኬታማ ለማድረግ በትብብር መስራት እንደሚገባ በክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

የጋምቤላ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 3ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በጋምቤላ ከተማ እያካሄደ ነው።

በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸኔ አስቲን በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በክልሉ የተገኘውን ሰላም በማጽናት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ስኬታማ ለማድረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር ይበልጥ በመቀራረብ ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

የህዝቦችንን አንድነትና አብሮነት የሚያጎለብቱ ገዥ ትርክቶችን በማጠናከር አሁን የተገኘውን ሰላም በማጽናት ረገድ በትብብር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የብዝሃ ሃሳብ አማራጮች እንዲጎለብቱ እየሰራ እንደሚገኝና በዘርፉም ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ደስታ ዲንቃ፤ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዘላቂ ሰላም፣ የህግ የበላይነትና የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲጎለብት የጎላ ሚና አላቸው ብለዋል።

የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ የተቋቋመበት ዓላማ በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተመካክረውና ተደጋግፈው የሚሰሩበትን ሁኔታ ለመጠናከር ታልሞ መሆኑን ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተወካይ አቶ ሳይመን ቱት፤ የጋራ ምክር ቤቱ ፓርቲዎች በክልሉ ብሎም በሀገራዊ ጉዳዮች በአንድነትና በትብብር ለመስራት አበርክቶው የጎላ ነው ብለዋል።

በተለይም ከሰባት ዓመት መዲህ የተፈጠረው ምቹ የፖለቲካ ምህዳር ፓርቲዎች ለህዝብና ለሀገር ጥቅም በጋራ እንዲሰሩ መልካም እድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላላ ጉባኤው በሚኖረው የአንድ ቀን ቆይታ ያለፉት ሁለት ዓመታት የስራ ክንውን ላይ በመወያየት ቀጣይ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ሲሆን፤ የጋራ ምክር ቤቱን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ እንደሚያካሂድም ይጠበቀል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም