ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ህብረተሰቡ በንቃት መሳተፍ አለበት - የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ባህርዳር፤ መጋቢት 26/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊዎች ለሀገራዊ መግባባት የጎላ ፋይዳ ያላቸውን ጉዳዮች በማንሳት በንቃት እንዲሳተፉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጠየቀ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በሰጡት መግለጫ፤ በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የአጀንዳ ማሳባሰቡ በክልሉ 267 ወረዳዎች የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመው በዚህም ከ4 ሺህ 500 በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ ተሳታፊዎች መለየታቸውን ገለጸዋል።

ከመጋቢት 27 እስከ ሚያዚያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በሚቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የማህበረሰብ ተወካዮችን ጨምሮ ተጽእኖ ፈጣሪ የማህበረስብ ክፍሎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያካተተ 6 ሺህ ወኪሎች ይሳተፋሉ ብለዋል።

የቅድመ ዝግጅት ስራው ስኬታማ እንደነበር ጠቅሰው፤ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱም የበለጠ ስኬታማ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ የሚሰበሰቡ አጀንዳዎች ለሀገራዋና ክልላዊ መግባባት የጎላ ፋይዳ እንዳለው በመረዳት ተሳታፊዎች የተሻሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እንዲወያዩ ጠይቀዋል።

ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ በሚከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት የተለያዩ ማህብረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ አካላት እንዲካተቱ ተደርጓል ብለዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰቡ ሒደት ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ተፈናቃይ ወገኖችና ሌሎች ወኪሎች እንደሚሳተፉም አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ቀደም ሲል በ10 ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ማከናወኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም