የጥልቅ ጉድጓድ ውሃን ለመስኖ ልማት መጠቀማችን በውስን መሬት ላይ ምርታማነታችን እንዲጨምር አድርጓል - የአሪ ዞን አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የጥልቅ ጉድጓድ ውሃን ለመስኖ ልማት መጠቀማችን በውስን መሬት ላይ ምርታማነታችን እንዲጨምር አድርጓል - የአሪ ዞን አርሶ አደሮች
ዲላ፤ መጋቢት 26/2017(ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአሪ ዞን አርሶ አደሮች ለመጀመሪያ ጊዜ የጥልቅ ጉድጓድ ውሃን ለመስኖ ልማት በመጠቀም በውስን የእርሻ መሬታቸው ምርታማነትን ማሳደጋቸውን ገለጹ።
የጉድጓድ ውሃ መስኖ ልማቱ በዓመት ሶስትና ከዚያ በላይ ጊዜ በማምረት ተጠቃሚነትን የማሳደግ ውጥንን ከማሳካት ባለፈ የገቢ ምንጭ በመጨመር ገበያን የማረጋጋት ሚናው የላቀ መሆኑ ተነግሯል።
በአሪ ዞን የባካ ዳውላ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ልሳኑ ፈረንጃ ለኢዜአ እንዳሉት በተያዘው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የጥልቅ ጉድጓድ ውሃ በመጠቀም በመስኖ ሽንኩርት ማልማታቸውን ተናግረው ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የደረሰ ምርታቸውን በማንሳት ለአካባቢ ገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው ከሩብ ሄክታር ማሳቸው እስከ 80 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።
የጥልቅ ጉድጓድ ውሃ የመስኖ ልማት ውሃ ገብ ከሆኑ አካባቢዎች ውጭ መስኖ መጠቀም እንደምንችል ያየንበት ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው አርሶ አደር ከበደ አዳነው ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረግነው ጥረት ውጤታማ አድርጎናል ብለዋል።
ከግማሽ ሄክታር በሚያንስ ውስን መሬታቸው ላይ የጥልቅ ጉድጓድ ውሃን በመጠቀም ያመረቱትን ቲማትም ለገበያ በማቅረብ ለቁፋሮ ያወጡትን ወጪ ሸፍነው ከ130ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን አስረድተዋል።
በቀጣይ በጥልቅ ጉድጓድ ውሃ መስኖ የሚሸፈን እርሻን በማስፋት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥና የገቢ ምንጭን ለማሳደግ ተግተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ሁሉንም የውሃ አማራጮች አሟጦ በመጠቀም ከ11 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት መቻሉን ያነሱት ደግሞ የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ ናቸው።
ከዚህ ውስጥም ለመጀመሪያ ጊዜ በ25 የጥልቅ ጉድጓድ ውሃ የመስኖ ስራ 157 ሄክታር መሬት ሽንኩርትና ቲማቲምን ጨምሮ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት በሄክታር ከ350 ኩንታል በላይ ምርት እየተገኘ ነው ብለዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትልና የእርሻ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ በበኩላቸው በክልሉ የከርሰና ገጸ-ምድር ውሃን ተጠቅሞ መስኖን የማልማት ልማድ እየተስፋፋ ነው ብለዋል።
በተያዘው ዓመትም ከእቅድ በላይ 142ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ልማት በሰብል በመሸፍን እስካሁን ከተሰበሰበ ሰብል ከ22 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ጠቅሰዋል።
ይህም በዓመት ሶስት ጊዜ እና ከዚያ በላይ በማምረት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ የተሰበሰበ ምርትን ለገበያ በማቅረብ የገበያ ማረጋጋት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።