ወጣት ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያን ቀዳሚ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ መስራት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ወጣት ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያን ቀዳሚ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ መስራት አለባቸው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2017(ኢዜአ)፦ወጣት ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያን ቀዳሚ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን በንቃት ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ተገለጸ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለወጣት ዲፕሎማቶች በኢንቨስትመንትና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ ዘመን ጁነዲን የኢትዮጵያን እምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮች ከልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ጋር አያይዘው አብራርተዋል።
በመንግስት የተተገበረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር እና በህንድ ውቅያኖስ አቅራቢያ ያላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርጋትም ገልጸዋል፡፡
በኢንቨስትመንት እና በዲፕሎማሲ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር፣ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ውጤታማ ለማድረግና ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች፣ ነጻ የንግድ ቀጣና እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ ከባለድርሻዎች ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝም የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።